Sunday, 13 July 2014

የየመን አወዛጋቢ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ ና የእንግሊዝ አቋም

ዜናው የአቶ አንዳርጋቸውን ንግግር ለአፍታ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱ ግን ግራ ያጋባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ‹‹እኔ አሁን ከራሴ ጋር ታርቄ ሰላም አግኝቻለሁ፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እኔ እንደ ምርቃት ነው የተቀበልኩት፡፡ አሁን የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም፡፡ ጥሩ ዕረፍት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በጣም በጣም ደክሞኛል … ሰልችቶኛል፡፡ እውነቴን ነው የምልህ ተረጋግቼ ያለሁበት ሁኔታ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጥላቻ በውስጤ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ብስጭት የለኝም፡፡ ምንም ዓይነት መጥፎ ስሜት አይሰማኝም፡፡ በቃ … የመጨረሻ እርጋታና ዕረፍት ውስጥ ነው ያለሁት፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከአንዴም ሁለቴ በፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ከሶ የሞት ፍርድ ባስፈረደ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው በጤናው ደስተኛነቱን አይናገርም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የንግግሩን አንድምታ በተመለከተ የተራራቀ መላምታቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለአንዳንዶች የአቶ አንዳርጋቸው ንግግር ባልተጠበቀ መንገድ በጠላቶቹ እጅ የወደቀ ሰው ያለበትን ሁኔታ ባለመቀበል የሰጡት ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ በአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያሰማ ላለው ሥጋት ምላሽ ለመስጠት መንግሥት አስገድዷቸው የሰጡት ቃል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልገሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰንዓ በኩል ወደ ኤርትራ ሊገቡ ሲል ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ በዚያው ዕለት ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን አስታውቋል፡፡ ይህ ከሁለት ሳምንት በላይ የዘለቀውን የአቶ አንዳርጋቸውን መገኛ ቦታ ጥያቄና መላምት የሚያስቆም ቢሆንም፣ በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ መያዝ ግለሰቡ ካላቸው የእንግሊዝ ዜግነት አኳያ የሚያስከትለው የሕግና የፖለቲካ አንድምታ ግን አሁንም የመወያያ አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡ በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የየመን፣ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግሥታት ሚና፣ ወቅታዊ ሁኔታና የመጪ ጊዜ ግንኙነት ግልጽ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ የሰጠችበት መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጠይቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ አይደለም በማለት እየተቿት ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ግንቦት 7 ለኢትዮጵያውያን መብትና ነፃነት እታገላለሁ እያለ በአመራሩ እርከን ከሊቀመንበሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመቀጠል የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው እንግሊዛዊ መሆናቸው ስሜት አልሰጣቸውም፡፡ በአንድ በኩል እንግሊዝ ዜጋዋ የሆነውን የአቶ አንዳርጋቸውን መብት ለማስጠበቅ ከየመንም ጋር ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጠበቅባትን አላደረገችም በሚል እየተተቸች ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ለሚሠራው ግንቦት 7 አመራር ዜግነት የሰጠችው እንግሊዝ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ሽብርተኝነት እንዲጠፋ ከኢትዮጵያ ጋር በጥምረት መሥራቷ የተቃርኖ ስሜት የፈጠረባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባለውን የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ግንኙነት አይጐዳውም ወይ ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእንግሊዝን ፓስፖርት የያዙ ግለሰብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ጥልቅ ያደርጋቸዋል? ዜግነታቸውን ጥለው ከሄዱ በኋላ ማንን ነው ነፃ የሚያወጡት? ይህ ዓይነቱ ድርጊትስ አንድን ሉዓላዊ አገር መዳፈር አይደለም ወይ? ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በዋና ጸሐፊነት ያገለግሉት የነበረው ግንቦት 7 በ2000 ዓ.ም. በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አማካይነት የተቋቋመ ሲሆን፣ አወዛጋቢው ምርጫ 97 የተካሄደበትን ቀን ለማስታወስ ስሙን እንደመረጠው ንቅናቄው ይገልጻል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተካሂዶ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ኢሕአዴግን በከፍተኛ ሁኔታ የተፎካከረው ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ፍፁም የበላይነት ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ቅንጅት በኋላ ላይ የአዲስ አበባን አስተዳደርና የፓርላማ መቀመጫውን አልረከብም ቢልም ዶ/ር ብርሃኑ የዋና ከተማዋ ከንቲባ እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫውን አጭበርብሯል በሚል ለተቃውሞና ለአመፅ የወጡ አካላት ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በፈጠሩት ግጭት ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ፣ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ የቅንጅት አመራሮች ታስረው የነበረ ሲሆን ዶ/ር ብርሃኑ ግንቦት 7ን የመሠረቱት ከእስር ቤት እንደተለቀቁ ከአገር ቤት ከወጡ በኋላ ነው፡፡
ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እታገላለሁ የሚል ቢሆንም፣ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለማስወገድ የትጥቅ ትግልን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት መንገድ እንደሚጠቀም ይገልጻል፡፡ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያው ወራት በግንቦት 7 መሪነት የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ ሲያደርጉ ነበር ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወቅቱ በአምስት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ሲወስን፣ በሌሎች 33 ግለሰቦች ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስኖ ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት የሞት ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
በወቅቱ በሌሉበት የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው አቶ አንዳርጋቸው ከቅጣቱ በኋላ ለቢቢሲ ‘ፎከስ ኦን አፍሪካ’ ፕሮግራም በሰጡት አስተያየት ቅጣቱን ጠብቀውት እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ይኼ ውሳኔ ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስገራሚ አይደለም፡፡ የነፃነትን ዋጋ እናውቃለን፡፡ መብቶቻችንን ለማስጠበቅ ሁሌም ቢሆን መስዋዕትነት ለመክፈል እንገደዳለን፡፡ ይኼ መስዋዕትነት የሞት ቅጣት ከሆነ እሱን በፀጋ እቀበላለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በዚያ ቃለ ምልልስ ንቅናቄው የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት የትጥቅ ትግልን ጭምር እንደ አማራጭነት እንደሚጠቀም አስታውቀው ነበር፡፡ ‹‹ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊሰማ እስካልፈቀደ ድረስ እንዲሰማንና ከሥልጣንም እንዲለቅ ለማድረግ የምናስገድደው ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡
በ2003 ዓ.ም. ፓርላማው በሽብርተኝነት ከፈረጃቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ግንቦት 7 ሲሆን ሌሎቹ ኦብነግ፣ ኦነግ፣ አልቃይዳና አልሸባብ ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በድጋሚ ተከሰው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት በድጋሚ የሞት ቅጣት ተላልፎባቸው ነበር፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያ ዓመት አካባቢ የኢሕአዴግ መሥራች ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አባል እንደነበሩ በጻፉት መጽሐፍ ገልጸዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. በገዛ ፈቃዳቸው ከኢሕአዴግ እንደለቀቁ ‹‹ነፃነትን የማያውቅ ‹‹ነፃ አውጪ››” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ላይ አትተዋል፡፡ በስደት ይኖሩበት ከነበረው እንግሊዝ በ1983 ዓ.ም. ተመልሰው የብአዴን አባልና በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ኮሚቴ አባል በመሆን እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ ማገልገላቸውን አስፍረዋል፡፡ በተለያዩ የአመለካከት ልዩነቶች ከኢሕአዴግ ጋር መለያየታቸውን የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው ከእነዚህ መካከል ኢሕአዴግ በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ላይ ያለው አቋም፣ የኤርትራ ሪፈረንደም፣ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አስተዳደር፣ የኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሙስና መበራከት፣ አቅምን መሠረት ያላደረገ የአባላትና የአመራር ምልመላና ዕድገት፣ በኢሕአዴግ ላይ ከማንም ነፃ በሆኑ ኦዲተሮች ዓመታዊ የሒሳብ ቁጥጥር አለመደረጉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ኢሳት በተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ የኢሕአዴግ አባል እንዳልነበሩ ደግሞ አስተባብለዋል፡፡
የየመን አወዛጋቢ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የመን በቁጥጥር ሥር አቶ አንዳርጋቸውን እንዳዋለች ወዲያው ለኢትዮጵያ መስጠቷን ያረጋገጠ ሲሆን የመን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ለእንግሊዝ ሳታስታውቅ በሚስጥር ለኢትዮጵያ አሳልፋ መስጠቷ ከዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ ትችት የሚያቀርቡባት አሉ፡፡ ነገር ግን የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠችው በ1991 ዓ.ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በቀድሞ የየመን ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ መካከል በሁለቱ አገሮች የሚፈለጉ ወንጀለኞችን አሳልፈው ለመስጠት ባደረጉት ስምምነት መሠረት እንደሆነ በመግለጽ ራሷን ትከላከላለች፡፡

No comments:

Post a Comment