Wednesday, 16 July 2014

16 JULY 2014 የመኢአድና የአንድነት የውህደት ጉዞ

                                         የመኢአድና የአንድነት የውህደት ጉዞ
ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫ 97ን ተከትሎ በወቅቱ ዋነኛ ተፎካካሪ በነበረው ቅንጅትና በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መካከል የምርጫውን ውጤት መሠረት በማድረግ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንግሥት ኃይልና ለተቃውሞ በወጡ ዜጐች መካከል በተፈጠረ ብጥብጥ ሳቢያ ከ200 በላይ ንፁኃን ዜጐች ሕይወት መቀጠፉ ይታወሳል፡፡

ለአጭር ጊዜ በተካሄደው ንቅናቄ የብዙኃን ኢትዮጵያውያንን ልብ መግዛት ችሎ የነበረው የአራት ፓርቲዎች ስብስብ የነበረው ቅንጅት፣ የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል በሚል ምክንያት ፓርላማ የመግባት ጥያቄውን መልሶ ለሕዝቡ አቀረበ፡፡ ይህን የፖለቲካ ውሳኔ ፓርቲው ራሱ መውሰድ ሲገባው ለምን መልሶ ወደ ሕዝብ አመጣው በሚል በበርካታ አካላት እስካሁንም ድረስ ይወቀሳል፡፡ 
መንግሥትም ምርጫው ተጭበርብሯል በተባለባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምርጫው እንዲደገም፣ ተጭበርብሯል የተባለው የምርጫ ውጤት ተቀባይነት እንዲያገኝና ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማ እንዲገቡ በርካታ ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች ሰጠ፡፡
ለወራት ከዘለቀው ከዚህ ሁሉ ንትርክና ጭቅጭቅ በኋላ ከምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ በጥቅምት ወር ዳግም ብጥብጥ ተቀሰቀሰ፡፡ ብጥብጡን ተከትሎ መንግሥት ጣቱን በወቅቱ የቅንጅት አመራሮች ላይ ሲቀስር፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ መንግሥት አላስፈላጊና ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል በሚል መንግሥትን ወነጀሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮችና አንዳንድ አባላት ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ የቅንጅትም ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገባ፡፡ 
አብዛኞቹ የቅንጅት መሪዎችና አባላትም ከሁለት ዓመት በላይ ታሰሩ፡፡ ከእስር በይቅርታ ሲፈቱ ገሚሶቹ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሄደው የተለያየ የትግል ሥልት እንደሚከተሉ ሲያስታውቁ፣ የተቀሩት ደግሞ የተለያዩ ፓርቲዎችን በማቋቋምና በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነትና በአመራርነት የትግል ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህም ክስተት በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ እንደ መልካምም እንደ መጥፎም ሒደት ተደርጐ የሚወሰድ ሆነ፡፡ ክስተቱን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚመለከቱት ጉዳዩን በኢትዮጵያ የምርጫና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሕዝቡ በያገባኛል ስሜት የተሳተፈበትና በምርጫ ካርድ መንግሥት መለወጥ እንደሚችል ማመኑን ሲሆን፣ መጥፎ ጐኑ ብለው የሚያነሱት ደግሞ የፓርቲው አመራሮች ከምርጫው በኋላ በወሰዱት ዕርምጃና አካሄድ በመከፋፈላቸው የተስፋውን ጭላንጭል ማጨለማቸውን በመጥቀስ ነው፡፡ 
የአንድነትና የመኢአድ ውህደት ሒደት
ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቅጥር ግቢ ውስጥ በርከት ያሉ ታዳሚዎች ድርጅቱ ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ሲያካሂደው የነበረው የውህደት ሒደት ፍሬ አፍርቶ ለቅድመ ውህደት ስምምነት መድረሱን ለመመልከት ተሰባስበዋል፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች አቶ አበባው መሐሪና ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሲጠበቅ የነበረውን የቅድመ ውህደት ስምምነት ተፈራርመው ይፋ አደረጉ፡፡ 
ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የተካሄደው የሁለቱ ፓርቲዎች የቅድመ ውህደት ስምምነት በተለያዩ አጋጣሚዎች የታጀበ ነበር፡፡ የመኢአድ አባላት ነን የሚሉ ግለሰቦች በቅድሚያ የውስጥ ችግራችንን እንፍታ በሚል ጥያቄ ባስነሱት አምባጓሮ፣ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. መንግሥት ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር በጋራ ሲሠሩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን አራት የፓርቲ አመራር አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የውህደት አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
የእርሳቸውን እስር ተከትሎ የሁለቱ ፓርቲዎች የውህደት አመቻች ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ የውህደቱ ሒደት በምንም ዓይነት ሁኔታ እንደማይደናቀፍ በመግለጽ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ሆን ተብሎ የሁለቱን ፓርቲዎች ውህደት የማደናቀፍ ሴራ ነው በማለት መንግሥትን ኮነነ፡፡ መንግሥት ለዚህ የሰጠው መልስ ደግሞ ዕርምጃው በምንም መንገድ ከምርጫም ሆነ ከሌላ ነገር ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለና ግለሰቦቹ የታሰሩት በሽብርተኝነት ወንጀል በመጠርጠራቸው ብቻ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
ከእስር ዕርምጃውም በኋላ የሁለቱ ፓርቲዎች የውህደት ሒደት በተሳካና በታቀደለት መሠረት እየተጓዘ እንደሆነ የሁለቱም ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ‹‹አሁን የውህደቱ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡ ብዙዎቹን ሥራዎች እያጠናቀቅን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐምሌ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔው ተጠርቶ ውህደቱ ተፈጻሚ ይሆናል፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የውህደት አመቻች ኮሚቴው ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ሁለቱ ፓርቲዎች ውህደቱን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የውህደት አመቻች ኮሚቴ በማቋቋም ሥራቸውን በዕቅዳቸው መሠረት በትጋት እየሠሩ ሲሆን፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ ሀብታሙ አያሌው ነበር፡፡ ኮሚቴው እንደሚያምነው ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሁለቱን ፓርቲዎች ውህደት ካለመፈለጉም በላይ፣ የተለያዩ ሁኔታዎችን በመጠቀም ለማደናቀፍ እንደሚሠራ እንገምታለን፤›› በማለት መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ 
ምንም እንኳን የአመቻች ኮሚቴው መግለጫ ይህን ቢልም፣ የሁለቱም ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች እንዳስረዱት የኮሚቴውን አባላት በማሰር ውህደቱ ላይ የሚያጠላው ምንም ዓይነት ነገር አይኖርም፡፡ 
ኢንጂነር ግዛቸው፣ ‹‹አንድ ፓርቲም ሆነ ማንኛውም ድርጅት ተቋማዊ አሠራር ይኖረዋል፤›› በማለት የአቶ ሀብታሙ አያሌው መታሰር ፓርቲው ተቋማዊ አሠራር የሚከተል በመሆኑ ያን ያህል ችግር እንደማይፈጥር ገልጸዋል፡፡ 
ኢንጂነሩ ሲቀጥሉም፣ ‹‹የአመራሮች ለተወሰነ ጊዜ በቦታቸው አለመኖር የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ቢኖረውም ያንን ሁኔታ ግን በተቋማዊ አሠራር እናስተካክለዋለን፤›› በማለት የአባላት መታሰር የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳለው ሆኖ ሥራዎች በታቀደለት መሠረት እየተካሄዱ እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ በበኩላቸው፣ ‹‹የልጁ መታሰር ቢያሳስበንም በውህደቱ ላይ የሚያስከትለው አንዳችም ነገር አይኖረውም፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ አሥር አባላት ያሉት የውህደት አመቻች ኮሚቴ የውህደቱን ሒደት የተመለከቱ የፋይናንስ፣ የሰነድ ዝግጅት፣ የሕዝብ ግንኙነትና የሎጂስቲክስ ሥራዎችን እንደሚሠራ የገለጹት ኢንጂነር ግዛቸው፣ ‹‹የሰነድ ዝግጅት ኮሚቴው አብዛኛውን ሥራውን አጠናቋል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ይህ ኮሚቴም የውህዱ ፓርቲን ፕሮግራምና ደንብ አዘጋጅቶ እንዳጠናቀቀ፣ ሐምሌ 19 እና 20 የሚካሄደውን የውህደት ሥራ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁንም አብራርተዋል፡፡ 
ፋይናንስን በተመለከተም፣ ‹‹የሚያስፈልገውን በጀት አውጥተን ያንን በጀት የምንሸፍንበትን መንገድና የገንዘብ ምንጭ እያፈላለግን ነው፤›› በማለት የውህደቱን ሒደት አስረድተዋል፡፡ 
ሐምሌ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሚካሄደው የውህደት ሥነ ሥርዓት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ የሁለቱ ፓርቲዎች አባላት መካከል 800 የሚሆኑ አባላት እንደሚገኙ የገለጹት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው፣ እነዚህ በርከት ያሉ አባላትን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት የሎጂስቲክስ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 
በ1997 ዓ.ም. ተነሳስቶ የነበረውን የሕዝብ መንፈስ እንመልሳለን በማለት እየሠሩ እንደሆነ የሚገልጹት ሁለቱ ፓርቲዎች፣ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው ዓይነት ስህተት እንዳይደገም ካለፈው ትምህርት መውሰዳቸውን በመጥቀስ፣ የሕዝቡን ተነሳሽነት እንደ አዲስ ለመመለስ እየሠሩ እንደሆነ በሚያወጧቸው መግለጫዎች አስረድተዋል፡፡ 
ሁለቱ ፓርቲዎችና ሌሎች ፓርቲዎች
የሁለቱ ፓርቲዎች ውህደት አመቻች ኮሚቴ ሌሎች ፓርቲዎችም ወደ ትብብር በመምጣት የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቃኘት በጋራ እንሥራ የሚል ጥሪ ለተለያዩ ፓርቲዎች ማስተላለፉን የሁለቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ መድረክ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የሁለቱን ፓርቲዎች ውህደት የሌሎች ፓርቲዎችን ግንኙነት በማይጐዳ ሁኔታ መካሄድ አለበት በማለት፣ የሁለቱ ፓርቲዎች የውህደት ሒደት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ከመጠየቁም በተጨማሪ፣ አንድነት እንደ መድረክ አባልነቱ የፓርቲውን ሕግና ደንብ አክብሮ እንዲሠራ አሳስቧል፡፡ 
የፓርቲውን ሕግና ደንብ አክብሮ የማይሠራ ከሆነ ከዚህ ቀደም ከወሰደው የቃላት ማስጠንቀቂያ የዘለለ ውሳኔ እንደሚወስድም አስታውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን የአንድነት ፕሬዚዳንት ለዚህ ጉዳይ ሲመልሱ፣ ‹‹ጉዳዩን የሚዲያ ምልልስ ማድረግ አንፈልግም፤›› ብለው ነገር ግን፣ ‹‹ይህንን ሁኔታ የምናየው አጠቃላይ የፓርቲዎች ትብብር አድርገን ነው፤›› በማለት የአንድነትና የመኢአድ ውህደት ማንንም ለመጉዳት ያላለመና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጠናከረ ሁኔታ በጋራ እንዲሠሩ ካለው ፅኑ ፍላጐት የመነጨ እንደሆነ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ 
‹‹እኛ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ ውህደት እንዲፈጥሩ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያካሄድን ነው፡፡ ውህደት ተፈጥሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አዲስ ፓርቲ መፈጠር አለበት የሚል እምነት በመያዛችን በእርሱ ላይ እየሠራን ነው፤›› ያሉት የአንድነት ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ውህደት የማይፈልጉ ፓርቲዎች ደግሞ ካሉ ከውህደቱ ባለፈ ሁኔታ በትብብር፣ በፕሮግራምና በፕሮጀክት አብረን ለመሥራት ሁልጊዜም ዝግጁ ነን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ቢሉም ግን ቀጣዩ የመድረክና የአንድነት ግንኙነት የሚወሰነው አዲስ በሚፈጠረው ውህዱ ፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ውህዱ ከተፈጸመ በኋላ የመኢአድም ሆነ የአንድነት ሕጋዊ ህልውናቸው ያከትማል፡፡ ያን ጊዜ አንድነት ስለሌለ በመድረክ በኩል ምንም የሚደረግ ነገር አይኖርም፤›› በማለት፣ በሁለቱ ፓርቲዎች መፃኢ ግንኙነት ላይ ወሳኝ የሚሆነው ውህዱ ፓርቲ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አቶ አበባው መሐሪ በበኩላቸው መዋሀድ ለሁሉም የሚጠቅም እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹መዋሀድ ይጐዳል ማለት ሞኝነት ይመስለኛል፤›› በማለት የመዋሀድን ጠቀሜታ ሲያስረዱ፣ እንደ ኢንጂነር ግዛቸው ሁሉ ሁለቱም ፓርቲዎች ውህደት የሚያካሂዱት በጋራ ለመሥራትና የተጠናከረ አንድ ኃይል ለመፍጠር እንጂ፣ የትኛውንም ተቃዋሚ ፓርቲን ለመጉዳት ባለመ መንገድ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉ ምሁራንና አስተያየት ሰጪዎች አብዛኞቹ ፓርቲዎች ውህደት፣ ቅንጅትም ሆነ ጥምረት ለመመሥረት ሲሠሩ የሚታዩት ምርጫ ሲቃረብ ነው በማለት የሚተቹ ሲሆን፣ የመኢአድና የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንቶች ግን ይህ ዓይነት አስተያየት እነሱን እንደማይወክል ይናገራሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ ፓርቲዎች የውህደት ድርድር የጀመሩት በመጪው ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳይሆን፣ ቀደም ብሎ ከአራት ዓመታት በፊት የተጀመረ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
በአገሪቱ ውስጥ በርከት ያሉ በጋራ የመሥራት ስምምነቶች በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ቢደረጉም፣ አብዛኞቹ የተነሱለትን ዓላማ ከግብ ሳያደርሱ ወደ መክሰም እንደሚያመሩ በመጥቀስ የሚተቹ ደግሞ፣ ብዙዎቹ ፓርቲዎች በጋራ የመሥራት ስምምነት የሚፈጽሙት ምርጫ ሲደርስ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የአንድነትና የመኢአድ የውህደት ሒደትም በአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚያስከትለውን ለውጥና የተለየ ውጤት የማምጣት ዕድል ወደፊት የሚገመገም እንደሆነም እነዚሁ ተቺዎች ይከራከራሉ፡፡        

No comments:

Post a Comment