Monday, 13 October 2014

“መፈንቅለ ዓለም ባንክ!” ኢትዮጵያን ኦባንግ በብቸኝነት ወክለዋል

      o at w b
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል የዓለም ባንክ በተለይ ከሲቪል ማኅበረሰቦች ጋር ሲያካሂድ የነበረው ስብሰባ “በመፈንቅለ ዓለም ባንክ” ተጠናቅቋል፡፡ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለምአቀፋዊ መድረኮች በመወከል ድምጻቸውን የሚያሰሙትኦባንግ “በመፈንቅሉ” ከተሳተፉት የዓለም ሲቪል ማኅበረሰቦች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡
የዓለም ባንክ ስለሚሰጠው ብድርና ዕርዳታ በተመለከተ ሊያካሂድ ያሰበው የፖሊሲ ለውጥ ሰነድ አፈትልኮ ከወጣ ጀምሮ በርካታ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሟገቱ ዓለምአቀፍ የሲቪል ማኅበረሰቦችን ያስቆጣ ሆኗል፡፡ የፖሊሲ ለውጡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው መልኩ ለታዳጊ አገራት ብድር ከመስጠት ባለፈ በተለይ አምባገነናዊ አገዛዝ በሰፈነባቸውና አገዛዞቹንም ለሚደግፉ ድርጅቶች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ገንዘብ መስጠትን የሚፈቅድ ነው፡፡
በዚህ አሠራር መሠረት ማንኛውም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለማድረግ የሚፈልግ ድርጅት ወደ አንድ ታዳጊ አገር ለመሥራት በሚፈልግበት ጊዜ ባንኩ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይጠይቅ ብድር ይፈቅድለታል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በዚያ ታዳጊ አገር ላይ የሰብዓዊ መብቶችን በመርገጥ፣ ከአምባገነናዊ ሥርዓቶች ጋር በመመሳጠር የፈለገውን ሕገወጥ ድርጊት ቢያከናውን የሚጠይቀው አይኖርም፤ ይህም እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ ብድሩን አያስከለክለውም፡፡
ለምሳሌ፤ መሬት ያለአግባብ ቢነጥቅ፣ ነዋሪዎችን ከቦታቸው ቢያፈናቅል፣ ለስደት ቢዳርግ፣ ህጻናትን በሥራ በማሰማራት “ባርነት” ቢያካሂድ፣ … ማንኛውንም ሰብዓዊ መብቶችን የሚረግጥ ሥራ ቢሰራ ለኢንቨስትመንት እስከተንቀሳቀሰ ድረስ ባንኩ ተጠያቂ አያደርገውም፤ ብድርም አይከለክለውም፡፡ ይህ አሁን ባንኩ ካለውና በበርካቶች ከሚተቸው አሠራሩ እጅግ መረን የለቀቀ ነው፡፡
የብሪክሶችን (BRICS – Brazil, Russia, India, China and South Africa) አሠራርና አካሄድ ለማክሸፍ የተነጣጠረ ነው የተባለለት ይህ የዓለም ባንክ ፖሊሲ ለውጥ ከ750 በላይ ዓለምአቀፍ የሲቪል ማኅበረሰቦች ተቃውመውታል፤ አሠራሩ እንዲቀየርም የማሻሻያ ፖሊሲዎችን ነድፈው አቅርበዋል፤ ለሳምንት ያህል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለባንኩ አመራሮች ገለጻ አድርገዋል፡፡
obang against land grabገና ከጅማሬው በስብሰባው ላይ በመገኘት የኢትዮጵያውያንን ድምጽ በብቸኝነት ሲያሰሙ የነበሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በስልክ በሰጡት አስተያየት ሳምንት የፈጀውን ስብሰባ አስረድተዋል፤ እርሳቸውም ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ካሩቱሪ እና የሼኽ አላሙዲ ሳውዲ ስታር መሰል የንግድ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር በኢትዮጵያ እያደረሱ ያሉት ግፍ ከበርካታ ማስረጃዎች ጋር የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት በተሰበሰቡበት ለባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ተወካይ የለም” እየተባለ በሚገመትበት ቦታ ሁሉበብቸኝነት አገራቸውን በመወከል የአገራቸውን ጉዳይ ለዓለምአቀፍ መድረክ በማቅረብ በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠራው “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ በኢትዮጵያ የሚካሄደው “የመሬት ነጠቃ” ሳይሆን “የህይወት ነጠቃ” ነው በማለት ተሰብሳቢውን የሲቪል ማኅበረሰብ ኃላፊዎች ያስደመመ፤ የባንኩ ባለሥልጣናትን አፍ ያስዘጋ መግለጫና ማብራሪያ በሳምንቱ የስብሰባ ቀናት ማቅረባቸውን ጎልጉል ያነጋገራቸው አንድ የሕንድ ሲቪል ማኅበረሰብና መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካ ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ተንከባካቢ ድርጅት ተወካዮች ተናግረዋል፡፡
የስብሰባው መጠናቀቂያ ቀን በነበረው ቅዳሜ ዕለት የሲቪል ማኅበረሰቦቹ ባንኩ በተግባር ላይ ሊያውል ያሰበውን ፖሊሲ ባቀረቡት የማሻሻያ ነጥቦች መሠረት የማይቀይር ከሆነ ስብሰባውን ረግጠው እንደሚወጡ በኢሜይል በላኩት መልዕክት ገልጸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከ750 በላይ የሲቪል ማኅበረሰቦች ኃላፊዎች እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት የመጨረሻ ቀን ስብሰባ ተቃሟቸውን እንዲያሰሙ ከተመረጡት መካከል ኦባንግ አንዱ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ከተናገሩት መካከል ባንኩ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው መልኩ፤ ስለ ሕዝብ የሚከራከሩ የሲቪል ማኅበረሰቦች እንዳይኖሩ በሕግ በተከለከለበት እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በህወሃት/ኢህአዴግ የተፈጠሩ የሃሰት “ሲቪል ማኅበረሰቦች” ባሉበትና እነርሱ በሚሰጡት የአንድ ወገንና አገዛዙን የሚደግፍ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ባንኩ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲረገጡ በመፍቀድ ፖሊሲዉን ለመቀየር የሚያደርገው አካሄድ የሚወገዝ መሆኑን በአጽዕኖት መናገራቸውን ለጎልጉል ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰቡ በገባው ስምምነት መሠረት የመጨረሻ ተናጋሪ ህንዳዊው የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካይo land grab ሶምያ ዱታ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም የሲቪል ማኅበረሰቡን ድምጽ የሚወክል የተቃውሞ ጽሁፍ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በንግግራቸውም ባንኩ የበርካታ ሕዝቦችን መብት የሚገፍፉ “የልማት” ተግባራትን ሲካሂድ እንደቆየ በመጥቀስ እንዲህ ያለውን አሠራር የሲቪል ማኅበረሰቦቹ ቢቃወሙም እስካሁን የተለወጠ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም ከዚህ አልፎ አሁን ደግሞ የአሰራር ለውጥ በማድረግ እጅግ በርካታ የዓለማችን ሕዝቦች የበለጠ ስቃይና መከራ እንዲደርስባቸው ባንኩ የፖሊሲውን ለውጥ እንዳያደርግ ሲወተውቱ መሰንበታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ለዚህ ሁሉ ውትወታ ባንኩ ጆሮ ዳባ ማለቱ እነዚህ ሁሉ በተሰበሰቡት ከ750 በላይ የሲቪል ማኅበረሰቦችና በሺዎች እነርሱ በሚወክሏቸው ስም የባንኩን ረቂቅ የማይቀበሉ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም የሕዝባቸውን መብቶች ለማስከበር ከዓለም ጋር እንጂ ከባንኩ ጋር እንደማይቆሙ በመናገር በውጭ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች ለመቀላቀል ስብሰባውን ረግጠው እንደሚወጡ ይፋ አደረጉ፡፡
ቀጥሎም ጥቁር የተቃውሞ ሸሚዞቻቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች በማሳየት ስብሰባውን አንድ በአንድ ረግጠው በመውጣት “መፈንቅለ ዓለም ባንክ” የተባለለትን ትዕይነት አሳዩ፡፡ ስብሰባውን የሚመሩት የዓለም ባንክ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በተከሰተው ትዕይንት ስብሰባውን መቀጠል ባለመቻላቸውና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ወሳኝ የነበረውን የዕለቱን ስብሰባ በይፋ ለመሰረዝ ተገድደዋል፡፡

No comments:

Post a Comment