Friday, 31 October 2014

ሰበር ዜና –አብርሃ ደስታ; ሀብታሙ አያሌው; የሽዋስ አሰፋ ; ዳንኤል ሺበሺ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው

 አብርሃ ደስታ የሁለት ድርጅቶች አባል ነው የሚል ክስ ተመስርቶበታል
• ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዟል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በልደታ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ምድብ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በተሰየመው ችሎት 10 ተከሳሾች በፌደራል አቃቢ ህግ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ100 ገጽ በላይ የክስ ቻርጅ የተነበበላቸው ሲሆን ከክስ ቻርጁ ጋር ከ300 ገጽ በላይ የምርመራ ሰነድ ቀርቦባቸዋል፡፡
የክሱ መዝገብ የተከፈተው ዘላለም ወርቃገኘሁ በተባለውና ‹‹የግንቦት 7 አመራር ነው፡፡›› ተብሎ ክስ በተመሰረተበት ግለሰብ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ የተካተቱትም፡-
1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ
5ኛ ተከሳሽ የሽዋስ አሰፋ
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ
9ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ደጉ
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው
ለሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ በፊት ክስ እንዳልደረሳቸውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በችሎቱ 6ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዮናታን ወልዴ በስተቀር ሁሉም ያለ ጠበቃ የቀረቡ ሲሆን ጠበቃዎቹ ያልቀረቡበት ምክንያትም ጠበቆቹ ደምበኞቻቸው የሚቀርቡበት ቦታና ጊዜ ስላልተነገራቸው እንዲሁም ቀደም ብለው እንዳይገናኙ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ ኃብታሙ አያሌው ችሎቱ ላይ ተናግሯል፡፡
ከሳሹ የፌደራል አቃቢ ህግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ጠቅሶ ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሶቹ በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጭብጥ ‹‹ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር በጋራ በመስራት›› የሚል ሲሆን ‹‹ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ የመንግስትን መሰረተ ልማት በማፈራረስ፣ ህዝብን ለአመጸ በማነሳሳት መንግስትን መለወጥ አላማው አድርጎ ከሚሰራውና ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር አባል በመሆንና በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ›› በሚል ቀርቧል፡፡
ሁለተኛው የክስ ጭብጥ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር በመሆን›› የሚል ሲሆን በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹የሽብር ቡድኑ አመራር በመሆንና አባል በመመልመል›› በሚል የክስ ጭብጥ ቀርቦበታልል፡፡
ከ2-5ኛ የክስ መዝገብ የሚገኙት ማለትም ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታና የሸዋስ አሰፋ ‹‹ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ከለላ በማድረግ ግንቦት 7 የተባለውን የሽብር ቡድን አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል የኔ ዓለምና ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በስልክ በመነጋገርና በማህበራዊ ድህረ ገጸ የተለያዩ መልዕክቶችን ተለዋውጠዋል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አብርሃ ደስታ ከግንቦት 7 በተጨማሪ ‹‹ደምኢት የተባለ ቡድን አባል ነው፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡
በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው ረቡዕ ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም 3 ሰዓት ተከሳሾቹ ዋስትና ይሰጣቸው አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ጠበቆች ጋር ተማክሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለተኛነት ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቀደም ሲል ለአራት ወራት ወደቆዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይመለሱ ፍርድ ቤቱን ስለጠየቁ ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (3ኛ) እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ ትናንት ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተወስደው የነበረ ቢሆንም እንደገና ወደማዕከላዊ ተመልሰው ከሰዓት እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡

Sunday, 26 October 2014

የኖርዌይ ኦስሎ ወጣቶች ስለአገራቸው ውይይት አካሄዱ


የዲሞክራሲ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የወጣቶች ክፍል ቅዳሜ ጥቅምት 10/2007 ዓም(ኦክቶበር 25/2014) “ለአገር እድገትና ለድሞክራሲ ግንባታ የወጣቶች አስትዋጾ” በሚል ሰፊ ውይይት ከ15:00 እስከ 18:00 ስዓት ተካሄደ። የመግቢያ ንግግሩ በድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት በአቶ አቢ  አማረ የውይይቱን ዓላማና አስፈላጊነት ለተሳታፊው በመግለጽ ወጣቶች ውይይቱ ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንዲካሄድ አጽንኦት ሰጠው ውይይቱ ቀጥሏል።

በመቀጠልም የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በአላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር መኖርና ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ  ከአንዱ ትውልድ ወደቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ፤ በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግደታ እንዳለበት፤ ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣  በምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ እንደሚችል ተረድቶ ወጣቱ ትውልድ በዓላማ፣ በቁርጠኝነት፣ በዕቅድና በመደራጀት  ለአገር እድገት፣ ነጻነት፣ፍትህና ዲሞክራሲ መታገልና ለውጥ ማምጣት እንዳለበት በክፍሉ ተወካይ በወጣት ይበልጣል ጋሹ ለውይይት እንደ መነሻ ባቀረበው ሃሳብ ላይ ገልጿል። እንዲሁም የወያኔን አስከፊ፣ ዘረኛና አምባገነናዊ ሥርዓት ለማስገወገድ  ወጣቱ ትውልድ የበኩሉን ሃላፊነት ወስዶ ይህን  ለአገርና ለህዝብ መቆም እንዳለበት በመግለጽ የውይይት ሃሳቦችን አስቀምጦ ስዓቱን ለውይይት ክፍት አድርጓል። በውይይቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወጣቱ ለክፉም ለመልካምም የራሱ የሆነ ትልቅ አገራዊ ታሪክ እንዳለው በመግለፅ  ወጣቱ እንዴት መታገልና ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ገንቢ አስትያየቶች፣ ምክሮችና አቅጣጫ ተሰጠዋል። ከተነሱትት ሃሳቦች መካከልም በበቂ ሁኔታ መደራጀት፣ በእውቀት እራስን ማብቃት፣ አገራዊ ስሜት መላበስ፣ታሪክን ጠንቅቆ ማዎቅ፣ አንድነት መፍጠር፣ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስልታዊ እቅድ መከተል፣ አቀራረባችንን እና ትኩረታችን መለየት፣ ቀጣይነት ያላቸው የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት እና ክፍሉን ማደራጀት ከተነሱት አበይት ሃሳቦች መካከል ነበሩ። በተጨማሪም ክፍሉ ከሌሎች የወጣት ህብረት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ልምድና ተሞክሮ  በመለዋወጥ ወጣቱን ይበልጥ ማንቃትና ፖለቲካዊ አድማሱን ማስፋትና የወያኔን ጨቋን መንግሥት ሊታገል የሚችልበትን አቅጣጫ ማሳየትና መንደፍ ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ተሰጦበታል። -

Monday, 13 October 2014

“መፈንቅለ ዓለም ባንክ!” ኢትዮጵያን ኦባንግ በብቸኝነት ወክለዋል

      o at w b
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል የዓለም ባንክ በተለይ ከሲቪል ማኅበረሰቦች ጋር ሲያካሂድ የነበረው ስብሰባ “በመፈንቅለ ዓለም ባንክ” ተጠናቅቋል፡፡ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለምአቀፋዊ መድረኮች በመወከል ድምጻቸውን የሚያሰሙትኦባንግ “በመፈንቅሉ” ከተሳተፉት የዓለም ሲቪል ማኅበረሰቦች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡
የዓለም ባንክ ስለሚሰጠው ብድርና ዕርዳታ በተመለከተ ሊያካሂድ ያሰበው የፖሊሲ ለውጥ ሰነድ አፈትልኮ ከወጣ ጀምሮ በርካታ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሟገቱ ዓለምአቀፍ የሲቪል ማኅበረሰቦችን ያስቆጣ ሆኗል፡፡ የፖሊሲ ለውጡ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው መልኩ ለታዳጊ አገራት ብድር ከመስጠት ባለፈ በተለይ አምባገነናዊ አገዛዝ በሰፈነባቸውና አገዛዞቹንም ለሚደግፉ ድርጅቶች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ገንዘብ መስጠትን የሚፈቅድ ነው፡፡
በዚህ አሠራር መሠረት ማንኛውም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለማድረግ የሚፈልግ ድርጅት ወደ አንድ ታዳጊ አገር ለመሥራት በሚፈልግበት ጊዜ ባንኩ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይጠይቅ ብድር ይፈቅድለታል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በዚያ ታዳጊ አገር ላይ የሰብዓዊ መብቶችን በመርገጥ፣ ከአምባገነናዊ ሥርዓቶች ጋር በመመሳጠር የፈለገውን ሕገወጥ ድርጊት ቢያከናውን የሚጠይቀው አይኖርም፤ ይህም እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ ብድሩን አያስከለክለውም፡፡
ለምሳሌ፤ መሬት ያለአግባብ ቢነጥቅ፣ ነዋሪዎችን ከቦታቸው ቢያፈናቅል፣ ለስደት ቢዳርግ፣ ህጻናትን በሥራ በማሰማራት “ባርነት” ቢያካሂድ፣ … ማንኛውንም ሰብዓዊ መብቶችን የሚረግጥ ሥራ ቢሰራ ለኢንቨስትመንት እስከተንቀሳቀሰ ድረስ ባንኩ ተጠያቂ አያደርገውም፤ ብድርም አይከለክለውም፡፡ ይህ አሁን ባንኩ ካለውና በበርካቶች ከሚተቸው አሠራሩ እጅግ መረን የለቀቀ ነው፡፡
የብሪክሶችን (BRICS – Brazil, Russia, India, China and South Africa) አሠራርና አካሄድ ለማክሸፍ የተነጣጠረ ነው የተባለለት ይህ የዓለም ባንክ ፖሊሲ ለውጥ ከ750 በላይ ዓለምአቀፍ የሲቪል ማኅበረሰቦች ተቃውመውታል፤ አሠራሩ እንዲቀየርም የማሻሻያ ፖሊሲዎችን ነድፈው አቅርበዋል፤ ለሳምንት ያህል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለባንኩ አመራሮች ገለጻ አድርገዋል፡፡
obang against land grabገና ከጅማሬው በስብሰባው ላይ በመገኘት የኢትዮጵያውያንን ድምጽ በብቸኝነት ሲያሰሙ የነበሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በስልክ በሰጡት አስተያየት ሳምንት የፈጀውን ስብሰባ አስረድተዋል፤ እርሳቸውም ከመሬት ነጠቃ ጋር በተያያዘ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ካሩቱሪ እና የሼኽ አላሙዲ ሳውዲ ስታር መሰል የንግድ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር በኢትዮጵያ እያደረሱ ያሉት ግፍ ከበርካታ ማስረጃዎች ጋር የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት በተሰበሰቡበት ለባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ተወካይ የለም” እየተባለ በሚገመትበት ቦታ ሁሉበብቸኝነት አገራቸውን በመወከል የአገራቸውን ጉዳይ ለዓለምአቀፍ መድረክ በማቅረብ በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠራው “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ በኢትዮጵያ የሚካሄደው “የመሬት ነጠቃ” ሳይሆን “የህይወት ነጠቃ” ነው በማለት ተሰብሳቢውን የሲቪል ማኅበረሰብ ኃላፊዎች ያስደመመ፤ የባንኩ ባለሥልጣናትን አፍ ያስዘጋ መግለጫና ማብራሪያ በሳምንቱ የስብሰባ ቀናት ማቅረባቸውን ጎልጉል ያነጋገራቸው አንድ የሕንድ ሲቪል ማኅበረሰብና መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካ ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ተንከባካቢ ድርጅት ተወካዮች ተናግረዋል፡፡
የስብሰባው መጠናቀቂያ ቀን በነበረው ቅዳሜ ዕለት የሲቪል ማኅበረሰቦቹ ባንኩ በተግባር ላይ ሊያውል ያሰበውን ፖሊሲ ባቀረቡት የማሻሻያ ነጥቦች መሠረት የማይቀይር ከሆነ ስብሰባውን ረግጠው እንደሚወጡ በኢሜይል በላኩት መልዕክት ገልጸው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከ750 በላይ የሲቪል ማኅበረሰቦች ኃላፊዎች እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት የመጨረሻ ቀን ስብሰባ ተቃሟቸውን እንዲያሰሙ ከተመረጡት መካከል ኦባንግ አንዱ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ከተናገሩት መካከል ባንኩ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለው መልኩ፤ ስለ ሕዝብ የሚከራከሩ የሲቪል ማኅበረሰቦች እንዳይኖሩ በሕግ በተከለከለበት እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በህወሃት/ኢህአዴግ የተፈጠሩ የሃሰት “ሲቪል ማኅበረሰቦች” ባሉበትና እነርሱ በሚሰጡት የአንድ ወገንና አገዛዙን የሚደግፍ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ባንኩ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲረገጡ በመፍቀድ ፖሊሲዉን ለመቀየር የሚያደርገው አካሄድ የሚወገዝ መሆኑን በአጽዕኖት መናገራቸውን ለጎልጉል ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰቡ በገባው ስምምነት መሠረት የመጨረሻ ተናጋሪ ህንዳዊው የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካይo land grab ሶምያ ዱታ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም የሲቪል ማኅበረሰቡን ድምጽ የሚወክል የተቃውሞ ጽሁፍ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በንግግራቸውም ባንኩ የበርካታ ሕዝቦችን መብት የሚገፍፉ “የልማት” ተግባራትን ሲካሂድ እንደቆየ በመጥቀስ እንዲህ ያለውን አሠራር የሲቪል ማኅበረሰቦቹ ቢቃወሙም እስካሁን የተለወጠ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም ከዚህ አልፎ አሁን ደግሞ የአሰራር ለውጥ በማድረግ እጅግ በርካታ የዓለማችን ሕዝቦች የበለጠ ስቃይና መከራ እንዲደርስባቸው ባንኩ የፖሊሲውን ለውጥ እንዳያደርግ ሲወተውቱ መሰንበታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ለዚህ ሁሉ ውትወታ ባንኩ ጆሮ ዳባ ማለቱ እነዚህ ሁሉ በተሰበሰቡት ከ750 በላይ የሲቪል ማኅበረሰቦችና በሺዎች እነርሱ በሚወክሏቸው ስም የባንኩን ረቂቅ የማይቀበሉ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም የሕዝባቸውን መብቶች ለማስከበር ከዓለም ጋር እንጂ ከባንኩ ጋር እንደማይቆሙ በመናገር በውጭ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች ለመቀላቀል ስብሰባውን ረግጠው እንደሚወጡ ይፋ አደረጉ፡፡
ቀጥሎም ጥቁር የተቃውሞ ሸሚዞቻቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች በማሳየት ስብሰባውን አንድ በአንድ ረግጠው በመውጣት “መፈንቅለ ዓለም ባንክ” የተባለለትን ትዕይነት አሳዩ፡፡ ስብሰባውን የሚመሩት የዓለም ባንክ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በተከሰተው ትዕይንት ስብሰባውን መቀጠል ባለመቻላቸውና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ወሳኝ የነበረውን የዕለቱን ስብሰባ በይፋ ለመሰረዝ ተገድደዋል፡፡

Friday, 10 October 2014

ጋጠ ወጡ ማን ነው?

    ጋጠ ወጡ ማን ነው?
የህወሃት ጉጅሌና ሎሌዎቹ መቼም ራሳቸውን የሚያይ አይንም መስታዎትም ያላቸው አይመስሉም። ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች በአጠገባቸው የዘሩ የማይመስሉት ለዚህ ሳይሆን ይቀራል። ምናልባትም ብልግና፣ ጭካኔ፣ ግፍ፣ አውሪያዊ ስብእና፣ ወገን ካለህግ መግደልና ማዋረድ፣ የህዝብ ሃብት በጠራራ ጸሃይ መዝረፍ ለእነሱ የተፈቀደና የተሰጠ ጸጋ አድርገው ሳይቆጥሩት ይቀራሉ?
ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰለጠነና የዳበረ ስርዓት አከባበር በሰፈነበት ከተማ ውስጥ ባልታጠቁ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ሲተኩሱና ሲያስተኩሱ በመዋላቸው ለደረሰባቸው ትዝብት የነውረኝነት ሀፍረት እንደማፈር ሰላማዊዎቹንና በሰላማዊ መንገድ እስከ ሲቪላዊ አልታዘዝም ባይነት መብት ያላቸውን ጠንቅቀው አወቀው የተንቀሳቀሱትን ዜጎች ጋጠ ወጥና ባለጌዎች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። ትንሽ ሲቀዠብርባቸው ደግሞ ኦባማ ስላነጋገረን የቀኑ ተቃዋሚዎች፣ ይህ አልበቃ ሲል ደግሞ የሻእቢያ ተላላኪዎች ሲሉም ተደምጠዋል። ከአውሬነት ብዙ ያልተለዩት ደጋፊዎቻቸው ተኩሱን ሲያንጣጣ የነበረው የቀድሞ የስዩም መስፍን የግል አሽከርና ሹፌር የነበረው ወዲ ወይኒ ግደይ ስለተባረረ ንዴታቸውን ከአደባባይ እንኳን መደበቅ አልቻሉም። እናስ እዚህ ውስጥ ጋጠወጡ ማነው? ሀገሩን የሚያስተዳድርበትን አራዊታዊና ህግ አልባ ስርአት በሰለጠነ ህዝብ ሀገር በአደባባይ ለኤግዚብሽን የሚያቀርብ መደዴ ወይስ እስከ ሲቪል እምቢተኝነት ድረስ ሊደርስ የሚችል መብታቸውን ጥንቅቀው የሚያውቁና በግፍ ስርአት ለሚኖረው ወገናቸው ድምጽ ያሰሙ የህዝብ ልጆች?
በዘሩ ታማኝነት ተመርጦ ከስዩም መስፍን ሾፌርነት ውጪ ቅንጣት የዲፕሎማሲ እውቀት የሌለውን ደንቆሮ የዲፕሎማት ማእረግና ሽጉጥ አስታጥቆ ዋሽንግተን ከሚልክ መንግስት በላይ ጋጠወጥና አጉራ ዘለል ከየት ይገኛል።
እውነቱ ግን ወዲህ ነው ያለው። ቢያንስ በነጻው አለምየሚኖሩ የኢትዮጵያ ልጆች በሀገራቸውና በወገናቸው ላይ በሚደርሰው ስቃይ ውርደትና ግፍ ተንገፍግፈዋል። የወያኔ ሹማምንት ግፋቸውን እንዲያቆሙ ያሰሩዋቸውን እንዲፈቱና ሀገር ዝርፊያ እስኪያቆሙ ድረስ በገቡበት እየገባ ቁም ስቅላቸውን ማሳየትና ጋጠወጥና የነውረኛ ስርአት አገልጋዮች መሆናቸውን ማጋለጡን ይገፉበታል። በሰሩት ወንጀል አለምአቀፍ ፍርድቤቶች መድረክ ላይ እየጎተተ የሚያቀርብበት ጊዜም ሩቅ አይደለም።
የወጋ ይርሳ እንደሆነ እንጂ የተወጋ አይረሳም። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሰላማዊ ተቃዋሚውን ድርጅት አባል በብረት ሶዶማዊ ምግባር የፈጸሙትን ጋጠ ወጥ የወያኔ ተላላኪዎች ማን ይረሳል። በየቤቱና በየጎዳናው በዱላ የሚቀጠቀጡትና ደማቸውን ሲጎርፍ ያየናቸው አዛውንት ሙስሊም ወገኖቻችን ደም እንዴት እንረሳለን። ሬሳቸው እንኳን ክብር አጥቶ የጋጠወጥ ወያኔ መጫወቻ የሆኑትን የኦጋዴን ወገኖቻችንን ማን ይረሳል። ጋምቤላ ጫካ ውስጥ እንደደኑ ተጨፍጭፈው የተቆለሉትን አኙዋኮች ማን ይረሳል። ከየኖሩበት ቦታ በግፍ እየተፈናቀሉ የሚንከራተቱትን እና የሚሞቱትን አማሮች ማን ይረሳል። በቆራጥነት ብቻ በሰላም መንገድ እንታገላለን ብለው በተነሱ ወህኒ የተወረወሩትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የታሰሩትንና የተሰደዱትን ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች የምንረሳቸው ስንሞት ብቻ ነው። ከየጎረቤት ሀገሩ እየታፈኑ የሚሰቃዩትን እነ አንዳርጋቸውን እና ሌሎች የሞቱትን ማን ይረሳል።
ህዝባችንን ወደ ሰላማዊ አመጽም ሆነ ወታደራዊ አመጽ እየገፋው ያለው ይህ የወያኔ ባህሪ ነው።
ግንቦት 7 ከዚህ አራዊታዊ ስርአት ጋር ሆናችሁ በተለያየ ምክንያት በህዝባችሁ ስቃይ ላይ የምትተባበሩ ወገኖች ሁሉ በአገኛችሁት አጋጣሚ ከእዚህ እኩይ ስርአት ተግባራት ራሳችሁን እንድታወጡ፣ ከቻላችሁ በውስጥም ሆናችሁ ወገናችሁን ሳትበድሉ ትግሉን እንድትቀላቀሉ ይመክራል።
መላው ህዝባችን በያለህበት ራስህን በራስህ እያደራጀህ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎችን ጀምር። በመላው አለም ዙሪያ ተሰደህ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለወገንህ ለራስህም ትንሳኤ ተነስ!!
ትግላችን የመጨረሻውን መጀመሪያ እየተያያዘ ነው። የትልቅ ሀገርና ትልቅ ህዝብ ባለቤቶች ስለሆንን ከወያኔ ወሮበላ ጉጅሌ በበለጠ የሚገባን ህዝብ ነን!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

የጎዛምን ወረዳ የሰማያዊ አመራሮች በገዥው ፓርቲ አፈና እየተደረገባቸው መሆኑን አስታወቁ

‹‹ወጣትና አርሶ አደሩ ‹‹ለምን ከሰማያዊ አባላት ጋር ታወራላችሁ እየተባለ ይታሰራል››
በምስራቅ ጎጃም ጎዛምን ወረዳ በአባሊባኖስ ቀበሌ የሰማያዊ ፓርቲ ቅርንጫፍ አመራሮችና አባላት፣ ‹‹ለምን የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሆናችሁ?›› በሚል ከፍተኛ አፈና እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
የወረዳው የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ አክሊሉ ውቤ፣ ወጣት ምህረት እንየውና አቶ አንመው ይዘንጋው ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጹት የወረዳና የቀበሌ ባለስልጣናት የሰማያዊ አመራሮችን ከሰማያዊ ፓርቲ እንዲወጡ እንደሚያስገድዷቸው ገልጸዋል፡፡
blue party
አቶ አንመው ይዘዘው የተባለውን የፓርቲው አባል መስከረም 14/2007 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ሚሊሻ ጥሩነህ መኮንን፣ ሚልሻ ሽታሁን ዘውዴ፣ ሚሊሻ አበባየሁ አባተ አስገድደው ወደ ቀበሌው ቢሮ በመውሰድ የቀበሌው ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በልስቲ ትዛዜ ከሰማያዊ ፓርቲ ካልወጣ እንደሚገረፍ፣ ካልሆነ አገር ጥሎ መሰደድ እንዳለበት እንደዛቱበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቀበሌው ሊቀመንበር ‹‹ኢህአዴግ በ1997 ምርጫ ቢሸነፍም ሰራዊቱም፣ ወታደሩም፣ ፖሊሱም፣ የኛ ነው፣ እናንተ ወረቀትና እስክርቢቶ ይዛችሁ ልታሸንፉ አትችሉም፤ አሁንም እርምጃ እንወስድባችኋለን›› በሚል እንደዛቱበትና ከፓርቲው እንዲወጣ እንዳስጠነቀቁት ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ አቶ አክሊሉ ውቤ የተባሉትን ግለሰብ ‹‹ቢያርፍ ይረፍ ከፖለቲካ ድርጅት መውጣት አለበት፣ ካላረፈ ለህይወቱ ያሰጋዋል›› በሚል የቀበሌው ሹም የሆኑት አቶ ገነነ እና አቶ በልስቲ ትዕዛዜ እንደዛቱባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ምህረቱ ይታየው የተባለው ወጣትም ተመሳሳይ ማስፈራሪያ እንደደረሰበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል አቶ በልስቲ ትዕዛዜ፣ ኮማንደር አንተነህ ፈንታሁን፣ አቶ ተሻገር አዲሱ የተባሉት የቀበሌው ባለስልጣናት ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ለምን ታወራላችሁ፣ ለምን ከእነሱ ጋር ትቆማላችሁ›› በሚል በየዕለቱ ወጣቱንና አርሶ አደሩን እንደሚያስሩ የወረዳው የፓርቲው ቅርንጫፍ አመራሮች ለነገረ ኢትዮጵያ አክለው ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ገዥው ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በከፈተባቸው ቦታዎች ቢሮዎችን ለመዝጋት፣ ቢሮ ለመክፈት እየጣረ በሚገኝባቸው ቦታዎች ደግሞ አባላቱንና አመራሮቹ ከፓርቲው እንዲወጡ ጫና እያደረገ እንደሚገኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡