Monday, 14 July 2014

በኖርዌ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እኔም እንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ በሚል ታላቅ ሕዝባዊ ውይይት አደረጉ

July 14/2014



ቅዳሜ ጁለይ 12/2014 በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አዘጋጅነት ሁላችንም እንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን በሚል አላማ በኖርዌ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የደንነት ሀይሎች መታፈንና ለአምባገነኑ የወያኔ መንግስት ታላልፈው መሰጠታቸውን በተመለከተ ወደ ፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከተለያዩ ከተሞች በመሰባሰብ በኖርዌ ኦስሎ ለአምስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት ሲያደርጉ ውለዋል::
ሕዝባዊ ውይይቱ ከቀኑ 15: 00 ሰአት ላይ የተጀመረ ሲሆን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኢትዮጵያኖች የአቶ እንዳርጋቸው ምስል ያለበትና ሁላችንም እንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን የሚል ጹሁፍ የተጻፉበትን ቲሸርት በመልበስ ለስብሰባው ድምቀት የሰጡት ሲሆን ለአቶ አንዳርጋቸው ያላቸውንም የትግል አጋርነት አስማስክራዋል እነዚህን ቲሸርቶች የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የበርገን ቅርንጫፍ በራሳቸው አነሳሽነት የሰሩ ሲሆን የድጋፍ ድርጅታችን ወጪውን በመሸፈን ለተሰብሳቢው በነጻ ኣድሏል።
ስብሰባውን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሕዝብ ግንኙነት አላፊ አቶ አቢ አማራ በሃያ ሶስት አመታት በወያኔ ጨካኝ አገዛዝ በግፍ ለተገደሉትና በግፍ ለሚሰቃይዩ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማስደረግ አስጀምረውታል በመቀጠልም አቶ ዮሀንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ ሊቀመንበር በስብሰባው ላይ የተገኛውን ሕዝብ እንኮን ደህና መጣችሁ በማለትና በማመስገን ፐሮግራሙን በንግግር የከፈቱት ሲሆን አቶ ዮሀንስ በንግግራቸው የወያኔ መንግስት በአቶ አንዳርጋቸው ላይ ባደረሰው አፈና ግንቦት 7 የክተት አዋጅ ማስተላለፉን ጠቅሰው አንባገነኑ የወያኔ መንግስት በአሁን ሰአት በሀገር ቤት በሰላማዊ ትግል እየታገሉ ባሉ ታጋዮች ላይ ሳይቀር እስር እያደረሰባቸው እንዳለ በማመልከት ሰሞንኑን እንኮን የሰመያዊ፣ የአንድነት፣ የአራና የፖለቲካ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ለስር ተዳርገዋል ብለዋል::
ስለሆነም ህዝባችንን ለእስር እያደረገ ያለውን አገዛዝ ለመቃወም ሁሉም በአንድነት መሰባሰብ እንዳለበት አጠንክረው በመናገር በአሁን ሰአት የአቶ አንዳርጋቸው በወያኔ መታፈንና መታሰር መላውን ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር እያንቀሳቀሰውና ሕዝቡም እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ በማለት በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቅሰው በአሁን ሰአት ትግሉ የግንቦት 7 ብቻ አይደለም ይህን ትግል በዚሁ አንድ ሆነን መቀጠል እለብን ብለዋል::
በመቀጠል አቶ ደባስ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አባል የአቶ አንዳርጋቸውን ከወጣት እድሜያቸው ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ አካሄድ አቶ እንዳርጋቸው ጽጌ ማን ነው ? በሚል ርእስ የአቶ አንዳርጋቸውን የትግል ጉዞ የሚዳስስ ዘገባ ሰፋ ባለ ትንታኔ በጹሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በስብሰባው ላይ የኢሀፓ ፣ የአርበኞች ግንባር፣ የሸንጎ ፣የስደተኛው ማህበር ተወካዮች እና ሌሎችም ሰዎች በየተራ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የየድርጅቷቹም ተወካዮች የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ መታፈንና ለእስር መዳረግን በተመለከተ የድርጅታቸውን አቋም ለተሰብሳቤው ያስረዱ ሲሆን የሁሉም ፖርቲ ተወካይች በአቶ አንዳርጋቸው መታፈንና ለእስር መደረግ ማዘናቸውን ገልጸው ሁሉም በአንድነት በመተባበር በማንኛውም የትግል እንቅስቃሴ የወያኔንን መንግስት ማስወገድ እንዳለባቸው አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል:

በየፕሮግራሞቹ መሀል ግጥሞችና ሌሏችም ፕሮግራሞች ቀርበው የመጀመሪያው ዞር ተጠናቋል::ከ30 ደቂቃ የእረፍት የሻይ እና የቡና ፕሮግራም በኋላ የሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ፕሮግራም በተያዘለት ጊዜ ተጀምሮ የፕሮግራሙን ተሳታፊዎች ያሰተፈ ፕሮግራም በአቶ አብዱ የሱፍ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ስታቫንገር ቅርንጫፍ ምክትል ሊቀመንበር ከግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪን ካብራሩ በኋላ ለተሰብሳቢው ለውይይት በማቅረብ በኖርዌ የምንኖር ኢትዮጵያኖች ይህን የትግል ጥሪ ለማስፈጸም ምን እናድርግ በማለት ለውይይት አቅርበው የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በአቶ ዮሀንስ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ ሊቀመንበር አወያይ አማካኝነት በስፋት ተወያይተውበታል ::
ተሰብሳቢውም በብዙ ነገሮች ከተወያዩ በኋላ ይሄ ግንቦት 7 ያወጣውን የመጀመሪያ እንከን የትግል ጥሪ ተግባራዊ በየቦታው አለም አቀፍ ታክስ ፎርሶች እየተቋቋሙ እንዳለና በኖርዌይም ይህንኑ ጥሪ ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቷች ያካተተ ታክስ ፎርስ እንዲቋቋም ተወስኖል:: በመቀጠልም በተሰብሰቢዎች በተመረጡ ሰዎች የተጻፋ ባለ ስድስት አሃዝ የተሰብሳቢው የአቋም መግለጫ ለጉባሄው በጹሁፍ ቀረቦል:: ተሰብሳቢው ያወጣው የአቋም መግለጫ
1. ሁላችንም አንዳርጋቸው ወይም አንድ አርጊያቸው ነን ስንል ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ በሐገራችን ኢትዮጵያ ለማስፈን የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን ማለታችን ነው።
2. የተለያዩ የፖለቲካና ሲቪክ ማህበራት የሚያደርጉትን መጠላለፍ እንዲቀርና በጋራ ወይም አንድ በመሆን እንዲሰሩ ግፊት እናደርጋለን።
3. ለሚቀርብልን ሐገርን የማዳን ጥሪ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን።
4. የየመን መንግስት ከአለም አቀፍ ህግ ጋራ የሚፃረር ስራ በመስራት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት የሰራውን ወንጀል ለዓለም አቀፍ ህግ የማቅረብ ስራ በጋራ እንደምንሰራ።
5. የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔ መታፈን ትግሉን የበለጠ እንደሚያጠናክረውና ወደ ውጤት እንዲያመራ የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን።
6. ወያኔ የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ኢትዮጵያውያንን እስርቤት ማስገባቱን እንዲቀርና የታሰሩትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ እንጠይቃለን በማለት የአቋም መግለጫ አውጥተዋል ።
በመጨረሻም አቶ ዳንሄል አበበ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ምክትል ሰብሳቢ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የአቋም መግለጫ ለተሰብሳቢው በጹሁፍ ያሰሙ ሲሆን በንግግራቸውም አቶ እንዳርጋቸው ጽጌ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት የቋሙ የነጻነት ታጋይ ናቸው እኔም እንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ የምንል ሁሉ ለሃያ ሶስት አመታት ህዝብን በዘረኝነት የከፋፈለውን ወያኔን በቃ ልንለው ይገባል ካሉ በኋላ በኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ አፈና፣ ግድያው፣ እስራቱ መጨመሩን በመናገር ይኼን ጨቋኝና አፋኝ ስርአት ለማስወገድ እንነሳ በማለት ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን በመጨረሻ እኔ እንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ እናንተስ በማለት የፕሮግራሙን ተሳታፊ በመጠየቅ ፕሮግራሙ በተያዘለት ሰዓት ከምሽቱ 20:00 ተጠናቋል ::
እኛ ሁላችንም እንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!

Ginbot 7 Press Release July 10 2014

የአቶ አዳርጋቸዉ መጋዝና እንድምታዉ

የአቶ አንዳርጋቸዉ መያዝ በተሰማ-በ16ኛዉ ቀን ባለፈዉ ማክስኞ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ ቴሊቪዥን ጣቢያ ባሠራጨዉ መግለጫ ግን «የአሸባሪ ድርጅት አመራርና በጥብቅ የሚፈለጉ » ያላቸዉ አቶ አንዳርጋቸዉ እና ሌሎች ሰዎች መታሰራቸዉን አረጋግጧል::
ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚሕ ቀደም ባሸባሪነት ወንጅሎ በሌሉበት ሞት ያስፈረደባቸዉ፤ የግቦት ሰባት የፍትሕ፤ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ ሰነዓ-የመን ተይዘዉ ወደ ኢትዮጵያ መጋዛቸዉ ብዙ እያነጋገረ ነዉ።አቶ አንዳርጋቸዉ የብሪታንያ ዜጋ ናቸዉ።
ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያንና የየመን መንግሥታትን እርምጃ አዉግዟል።የብሪታንያ መንግሥት በበኩሉ የየመን መንግሥት አቶ አዳርጋቸዉን ለኢትዮጵያ አሳልፎ መስጠቱን የጄኔቫ-ሥምምነትን የጣሰ ብሎታል።በአቶ አንዳርጋቸዉ ላይ ግርፋት ወይም ሌላ በደል እንዳይፈፀምባቸዉ፤ ከኤምባሲና ከሕግ ባለሙያዎች ጋር የመነጋገር መብታቸዉ እንዲጠበቅ ጠይቋል።በተለይ በሌሉበት የተወሰነባቸዉ የሞት ቅጣት እንዳይፀና አሳስቧል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል፤ ሑዩማን ራይትስ ዋች እና ሌሎች የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም አቶ አንዳርጋቸዉ መጋዛቸዉን ተቃዉመዉ፤ «ሰብአዊ ምብት ይጥሳል» የሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸዉን ያሰቃያል ብለዉ እንደሚሰጉ እያስታወቁ ነዉ።
Die Gesellschaft für bedrohte Völker(ለተበደለ ሕዝብ ተሟጋች ማሕበር እንደማለት ነዉ) የተሰኝዉ የጀርመን የመብት ተሟጋች ድርጅት ደግሞ አቶ አንዳርጋቸዉን ለማስፈታት የአዉሮጳ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቋል።አዉሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ በየከተማዉ ባደረገዉ የተቃዉሞ ሠልፍ የአቶ አንዳርጋቸዉን መያዝና መጋዝ አዉግዟል።የኢትዮጵያ መንግሥትን ባለሥልጣናትን ሥለ ጉዳዩ ለማነጋገር፤ ቢቻል በዚሕ ዉይይት እንዲሳተፉ ለመጋበዝ ለተከታታይ ቀናት ሞክረን ነበር-ያገኘናቸዉ እስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም።ሌሎቹ ን ልናገኛቸዉ አልቻልንም።
የአቶ አንዳርጋቸዉ መያዝ በተሰማ-በ16ኛዉ ቀን ባለፈዉ ማክስኞ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ ቴሊቪዥን ጣቢያ ባሠራጨዉ መግለጫ ግን «የአሸባሪ ድርጅት አመራርና በጥብቅ የሚፈለጉ » ያላቸዉ አቶ አንዳርጋቸዉ እና ሌሎች ሰዎች መታሰራቸዉን አረጋግጧል።በአምደ መረብ የሚፃፈዉ ዉግዘት፤ ክርክርም፤ እንደቀጠለ ነዉ።የእርምጃዉ ሕጋዊ፤ ሠብኣዊና ፖለቲካዊ እድምታ የዛሬ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

Sunday, 13 July 2014

የየመን አወዛጋቢ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ ና የእንግሊዝ አቋም


ዜናው የአቶ አንዳርጋቸውን ንግግር ለአፍታ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱ ግን ግራ ያጋባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ‹‹እኔ አሁን ከራሴ ጋር ታርቄ ሰላም አግኝቻለሁ፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እኔ እንደ ምርቃት ነው የተቀበልኩት፡፡ አሁን የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም፡፡ ጥሩ ዕረፍት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በጣም በጣም ደክሞኛል … ሰልችቶኛል፡፡ እውነቴን ነው የምልህ ተረጋግቼ ያለሁበት ሁኔታ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጥላቻ በውስጤ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ብስጭት የለኝም፡፡ ምንም ዓይነት መጥፎ ስሜት አይሰማኝም፡፡ በቃ … የመጨረሻ እርጋታና ዕረፍት ውስጥ ነው ያለሁት፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከአንዴም ሁለቴ በፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ከሶ የሞት ፍርድ ባስፈረደ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው በጤናው ደስተኛነቱን አይናገርም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የንግግሩን አንድምታ በተመለከተ የተራራቀ መላምታቸውን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለአንዳንዶች የአቶ አንዳርጋቸው ንግግር ባልተጠበቀ መንገድ በጠላቶቹ እጅ የወደቀ ሰው ያለበትን ሁኔታ ባለመቀበል የሰጡት ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ በአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያሰማ ላለው ሥጋት ምላሽ ለመስጠት መንግሥት አስገድዷቸው የሰጡት ቃል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልገሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሰንዓ በኩል ወደ ኤርትራ ሊገቡ ሲል ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ በዚያው ዕለት ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን አስታውቋል፡፡ ይህ ከሁለት ሳምንት በላይ የዘለቀውን የአቶ አንዳርጋቸውን መገኛ ቦታ ጥያቄና መላምት የሚያስቆም ቢሆንም፣ በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ መያዝ ግለሰቡ ካላቸው የእንግሊዝ ዜግነት አኳያ የሚያስከትለው የሕግና የፖለቲካ አንድምታ ግን አሁንም የመወያያ አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡ በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የየመን፣ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግሥታት ሚና፣ ወቅታዊ ሁኔታና የመጪ ጊዜ ግንኙነት ግልጽ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ የሰጠችበት መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጠይቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ አይደለም በማለት እየተቿት ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ግንቦት 7 ለኢትዮጵያውያን መብትና ነፃነት እታገላለሁ እያለ በአመራሩ እርከን ከሊቀመንበሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመቀጠል የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው እንግሊዛዊ መሆናቸው ስሜት አልሰጣቸውም፡፡ በአንድ በኩል እንግሊዝ ዜጋዋ የሆነውን የአቶ አንዳርጋቸውን መብት ለማስጠበቅ ከየመንም ጋር ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የሚጠበቅባትን አላደረገችም በሚል እየተተቸች ነው፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ለሚሠራው ግንቦት 7 አመራር ዜግነት የሰጠችው እንግሊዝ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ሽብርተኝነት እንዲጠፋ ከኢትዮጵያ ጋር በጥምረት መሥራቷ የተቃርኖ ስሜት የፈጠረባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባለውን የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ግንኙነት አይጐዳውም ወይ ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእንግሊዝን ፓስፖርት የያዙ ግለሰብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ጥልቅ ያደርጋቸዋል? ዜግነታቸውን ጥለው ከሄዱ በኋላ ማንን ነው ነፃ የሚያወጡት? ይህ ዓይነቱ ድርጊትስ አንድን ሉዓላዊ አገር መዳፈር አይደለም ወይ? ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በዋና ጸሐፊነት ያገለግሉት የነበረው ግንቦት 7 በ2000 ዓ.ም. በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አማካይነት የተቋቋመ ሲሆን፣ አወዛጋቢው ምርጫ 97 የተካሄደበትን ቀን ለማስታወስ ስሙን እንደመረጠው ንቅናቄው ይገልጻል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተካሂዶ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ኢሕአዴግን በከፍተኛ ሁኔታ የተፎካከረው ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ፍፁም የበላይነት ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ቅንጅት በኋላ ላይ የአዲስ አበባን አስተዳደርና የፓርላማ መቀመጫውን አልረከብም ቢልም ዶ/ር ብርሃኑ የዋና ከተማዋ ከንቲባ እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫውን አጭበርብሯል በሚል ለተቃውሞና ለአመፅ የወጡ አካላት ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በፈጠሩት ግጭት ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ፣ ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ የቅንጅት አመራሮች ታስረው የነበረ ሲሆን ዶ/ር ብርሃኑ ግንቦት 7ን የመሠረቱት ከእስር ቤት እንደተለቀቁ ከአገር ቤት ከወጡ በኋላ ነው፡፡
ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እታገላለሁ የሚል ቢሆንም፣ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለማስወገድ የትጥቅ ትግልን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት መንገድ እንደሚጠቀም ይገልጻል፡፡ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2002 ዓ.ም. የመጀመሪያው ወራት በግንቦት 7 መሪነት የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ ሲያደርጉ ነበር ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወቅቱ በአምስት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ሲወስን፣ በሌሎች 33 ግለሰቦች ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስኖ ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት የሞት ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
በወቅቱ በሌሉበት የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው አቶ አንዳርጋቸው ከቅጣቱ በኋላ ለቢቢሲ ‘ፎከስ ኦን አፍሪካ’ ፕሮግራም በሰጡት አስተያየት ቅጣቱን ጠብቀውት እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ይኼ ውሳኔ ለእኛም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስገራሚ አይደለም፡፡ የነፃነትን ዋጋ እናውቃለን፡፡ መብቶቻችንን ለማስጠበቅ ሁሌም ቢሆን መስዋዕትነት ለመክፈል እንገደዳለን፡፡ ይኼ መስዋዕትነት የሞት ቅጣት ከሆነ እሱን በፀጋ እቀበላለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በዚያ ቃለ ምልልስ ንቅናቄው የሚፈልገውን ውጤት ለማምጣት የትጥቅ ትግልን ጭምር እንደ አማራጭነት እንደሚጠቀም አስታውቀው ነበር፡፡ ‹‹ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊሰማ እስካልፈቀደ ድረስ እንዲሰማንና ከሥልጣንም እንዲለቅ ለማድረግ የምናስገድደው ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡
በ2003 ዓ.ም. ፓርላማው በሽብርተኝነት ከፈረጃቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ግንቦት 7 ሲሆን ሌሎቹ ኦብነግ፣ ኦነግ፣ አልቃይዳና አልሸባብ ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በድጋሚ ተከሰው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው በሌሉበት በድጋሚ የሞት ቅጣት ተላልፎባቸው ነበር፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያ ዓመት አካባቢ የኢሕአዴግ መሥራች ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አባል እንደነበሩ በጻፉት መጽሐፍ ገልጸዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም. በገዛ ፈቃዳቸው ከኢሕአዴግ እንደለቀቁ ‹‹ነፃነትን የማያውቅ ‹‹ነፃ አውጪ››” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ላይ አትተዋል፡፡ በስደት ይኖሩበት ከነበረው እንግሊዝ በ1983 ዓ.ም. ተመልሰው የብአዴን አባልና በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ኮሚቴ አባል በመሆን እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ ማገልገላቸውን አስፍረዋል፡፡ በተለያዩ የአመለካከት ልዩነቶች ከኢሕአዴግ ጋር መለያየታቸውን የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው ከእነዚህ መካከል ኢሕአዴግ በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ላይ ያለው አቋም፣ የኤርትራ ሪፈረንደም፣ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አስተዳደር፣ የኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የሙስና መበራከት፣ አቅምን መሠረት ያላደረገ የአባላትና የአመራር ምልመላና ዕድገት፣ በኢሕአዴግ ላይ ከማንም ነፃ በሆኑ ኦዲተሮች ዓመታዊ የሒሳብ ቁጥጥር አለመደረጉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ኢሳት በተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ የኢሕአዴግ አባል እንዳልነበሩ ደግሞ አስተባብለዋል፡፡
የየመን አወዛጋቢ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የመን በቁጥጥር ሥር አቶ አንዳርጋቸውን እንዳዋለች ወዲያው ለኢትዮጵያ መስጠቷን ያረጋገጠ ሲሆን የመን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ለእንግሊዝ ሳታስታውቅ በሚስጥር ለኢትዮጵያ አሳልፋ መስጠቷ ከዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ውጪ እንደሆነ በመጥቀስ ትችት የሚያቀርቡባት አሉ፡፡ ነገር ግን የመን አቶ አንዳርጋቸውን ለኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠችው በ1991 ዓ.ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በቀድሞ የየመን ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳላህ መካከል በሁለቱ አገሮች የሚፈለጉ ወንጀለኞችን አሳልፈው ለመስጠት ባደረጉት ስምምነት መሠረት እንደሆነ በመግለጽ ራሷን ትከላከላለች፡፡
‘ዘ ኢኮኖሚስት’ መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ ግን የመን አሳልፎ መስጠቱን ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ተገቢነት ያላቸው ሥነ ሥርዓቶችን አልፈጸመችም፡፡ ለእንግሊዝ ባለሥልጣናት ቀድማ ሳታሳውቅ አሳልፋ መስጠቷ አንዱ ጥሰት እንደሆነም ጠቅሷል፡፡ መጽሔቱ ያነጋገራቸው አናንድ ዱባይ የተሰኙ ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ሕግ ኤክስፐርት ቅድሚያ የማሳወቅ ሥነ ሥርዓት በቪዬና የኮንሱላር ግንኙነቶች ኮንቬንሽን የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የመን ለእንግሊዝ ኤምባሲ ሳታሳውቅ አሳልፋ መስጠቷ ሕጉን እንድትጥስ እንዳደረጋት አስረድተዋል፡፡
የሒዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ በበኩላቸው የየመንና የኢትዮጵያ ድርጊት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሕግ በሚጥልባት ግዴታ መሠረት አቶ አንዳርጋቸው በጠበቃቸው፣ በቤተሰባቸውና በእንግሊዝ ኮንሱላር ኃላፊዎች እንዲጐበኙ ማድረግ እንዳለባት ጠይቀዋል፡፡ የመንም ምንም ዓይነት የቅድመ አሳልፎ መስጠት ሥነ ሥርዓቶችን ሳትጠብቅ ወዲያውኑ ለኢትዮጵያ አሳልፋ መስጠቷ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡
ሌፍኮ የመን ግርፋትን ለማስቀረት የተፈረመው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አፅዳቂ መሆኗን አስታውሰው፣ በኮንቬንሽኑ ተላልፎ የሚሰጠው ወንጀለኛ ለግርፋት የሚጋለጥ ስለመሆኑ በቂ ምክንያት ካለ አሳልፎ የመስጠት ውሳኔው ሊቀር እንደሚገባ የተደነገገ ቢሆንም፣ የመን ይህን ችላ በማለት አሳልፋ መስጠቷም ሌላ ጥሰት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ሌፍኮ የኮንቬንሽኑ ድንጋጌ ኢትዮጵያና የመን ወንጀለኛን አሳልፎ ለመስጠት ከፈጸሙት ስምምነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ተከራክረዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የየመን ባለሥልጣናት መረጃ እንዲሰጡት በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ እንዳጣ በመግለጽ ሥጋት እንደገባው አስታውቆ ነበር፡፡ ድርጊቱም ከቪዬና ኮንቬንሽን ተፃራሪ እንደሆነ አመልክቶ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ቢሮው አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ አስቀድሞ የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው አስታወሶ እንግሊዝ በመርህ ደረጃ የሞት ቅጣትን ስለምትቃወም ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ እንዳታደርግ ጠይቋል፡፡
ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርት የየመን ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግን ስለመጣሱና አለመጣሱ ለመግለጽ የአገሪቱን ብሔራዊ ሕግና በኢትዮጵያና በየመን መካከል ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት የተፈራረሙትን ስምምነት በቅድሚያ ማጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የመንና ኤርትራ በሃኒሽ ደሴቶች ጉዳይ ግጭት ውስጥ ስለሆኑ ኤርትራን ለመጉዳት አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ መስጠቷን በመግለጽ የመን ሕጋዊ ግዴታዋን ለመወጣት አለመሞከሯን የሚተቹም አሉ፡፡
የእንግሊዝ አቋም
ታዋቂው ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትን ጨምሮ በርካታ ተንታኞች በጉዳዩ ላይ የእንግሊዝ ድምፅ በጉልህ አለመሰማቱን ተችተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ዜጋው ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዳይሰጡ የውጭ ጉዳይ ቢሮው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አለማድረጉን በመኮነን በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው አስቀድሞ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ ልታደርግ ትችላለች በሚል ሥጋት የገባቸው አሉ፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮም ኢትዮጵያ ቅጣቱን ተግባራዊ እንዳታደርግ ጠይቋል፡፡
የግንቦት 7 ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማደቦ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ የምሥራች ኃይለ ማርያምና በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ልዑካን በመምራት መጥተው የነበሩትና አሁንም የአውሮፓ ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጎሜዝ፣ በተለያዩ ሚዲያዎች የእንግሊዝ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን አነስተኛ ትኩረት አውግዘዋል፡፡ አንዳንድ የእንግሊዝ ሚዲያዎች እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸውን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ዘግበዋል፡፡
እንግሊዝና ኢትዮጵያ አብረው ከሚሠሯቸው ነገሮች መካከል ዋነኛው በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን መዋጋት መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ ከሚያሴረውና በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ግንቦት 7 አመራሮች መካከል አንዱ ለሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዜግነት መስጠቱ ያልተዋጠላቸው አካላት፣ ጉዳዩ የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳያበላሽ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከርም የአቶ አንዳርጋቸውን ዜግነት መሰረዝ እንዳለባትም የጠየቁ አሉ፡፡
እንደ ቀደመው ጊዜ ሌላው አገር ለሚያራምደው ፖሊሲ ተቃውሞ ለማሳየት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት ዜግነቱን ለአቶ አንዳርጋቸው እንግሊዝ የሰጠች እንደሚመስላቸው የገለጹት ኤክስፐርቱ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ዜግነት የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጐዳል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡ አሁን የአቶ አንዳርጋቸውን ዜግነት መሰረዝ ለእንግሊዝ ቀላል እንደማይሆንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የግለሰቡ ፖለቲካዊ ባህርይ በተለይም ዜግነት የሰጠውን አገር የሚጐዳ ተግባር መፈጸሙ ዜግነቱን ለመሰረዝ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በተያያዘ መጠየቅ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ እንግሊዝ ግንቦት 7 እንዴት ነው የምትወስደው የሚለው ነው፡፡ ዜግነት ጥቅም ብቻ ሳሆን ግዴታም አለው፡፡ ዜግነት ለሰጠህ አገር ታማኝ መሆን አለብህ፡፡ የግለሰቡ እንቅስቃሴ ከዚያ አገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር ሊፃረር አይገባም፡፡ ይኼ የግንቦት 7 ድርጊት ከእንግሊዝ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ነው ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ አቶ አንዳርጋቸው በሽብርተኛነት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ነገር ግን እንግሊዝ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ለሽብርተኝነት የሰጠው ትርጉም በጣም ሰፋ ብሎ መተርጐሙ ላይ ተቃውሞ እንዳላት በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ ድንገት ያለመግባበት ምክንያት ሊሆን አይችልም፤›› ሲሉም ኤክስፐርቱ ይደመድማሉ፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ፖለቲካው ከዓለም አቀፍ ሕግ የበለጠ የሚመዝን በመሆኑ፣ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ ግንኙነት ዙሪያ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማይኖረው አመልክተዋል፡፡
ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሱት በቅርቡ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተነጋገሩትን የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ሊኔ ፊዘርስቶንን ነው፡፡ ሚኒስትሯ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አገራቸው በየዓመቱ የምትሰጠውን 300 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የልማት ድጋፍ አጠናክራ መቀጠልዋን ማስታወቃቸው፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከምንም ነገር በላይ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዓርብ ምሽት ከቢቢሲ ‹‹ፎከስ ኦን አፍሪካ›› ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ የሞት ፍርዱ ተፈፃሚ ይሆናል ወይ ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አሁን መናገር አልችልም›› በማለት ከማረጋገጥ የተቆጠቡ ሲሆን፣ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያን የኤርትራ መልዕክተኛ ሆነው የመበጥበጥ ሥራ እስከሠሩ ድረስ የእንግሊዝ ዜጋ መሆናቸው እሳቸውን በቁጥጥር ለማዋል ኢትዮጵያ ያለባትን የሞራልና የሕግ ግዴታ እንደማያስተጓጉለው ገልጸዋል፡፡ በሌሉበት ስለተፈረደባቸው በድጋሚ ጉዳያቸው እንዲታይ ይደረጋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ  ‹‹በአገር ከሌሉ ምን ማድረግ እንችላለን›› ያሉ ሲሆን ጉዳዩ በድጋሚ ሊታይ እንደማይችል ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

ወያኔ አንዳርጋቸው ያፈነበት እለት የሚረግምበት ቀን ሩቅ አይደለም!

                                                                        
የህወሃት ጉጅሌ እንደማንኛውም አምባገነን ከፊት ከነበሩ አምባገነኖች ቅንጣት ትምህርት አልተማረም። ወያኔዎች በእብሪት የያዙት ስልጣንና ከህዝብ የዘረፉትን ንብረት የሚያጡት እየመሰላቸው በባነኑ ቁጥር የነጻነት አርበኞችን በማፈን በመግደልና በማሰቃየት ፍርሃታቸው የተወገደ ይመስላቸዋል።
ወያኔ የእኛ መሪና የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት አርበኛ በሆነው አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ያካሄደው አፈና ከአፈናውም በሆላ በሚያደርሱበት አካላዊ ስቃይ ፍርሃታቸው የሚወገድ ወይም ስርአታቸው ከሞት የሚተርፍ መስሏቸው ከሆነ በእጅጉ ተሳስተዋል። አንዳርጋቸው ዛሬ በእጃቸው ሆኖ በነጻነት ይኖር ከነበረበት በበለጠ የሚለበልባቸው የውስጥ እግር እሳት ይሆናል።
አንዳርጋቸው ሰበአዊ ምቾቱንና ለራሱና ለቤተሰቡ መኖርን አቁሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻነት በህይወቱ ሊጋፈጥ ከቆረጠ ቆይቷል። እኛ የትግል ጓዶቹና ለህዝብ ነጻነት የቆሙ ሃይሎች ሁሉ አንዳርጋቸውን እናውቀዋለን። ወያኔ በአካሉ ላይ የለመደውን ስቃይ ጀምሮበታል፣ ከዚህ የበለጠም ጉዳት እንደሚያደርስበትም እናውቃለን። የአንዳርጋቸውን ታላቅ የነጻነት ሰውነትና ክብረ ህሊናውን፣ በአርበኝነቱ የሚሰማውን የኩራት ስሜቱን ለግፈኞች ያለውን ንቀትና መጸየፍ ሊለውጡ እንደማይችሉ አስረግጠን እናውቃለን።
አንዳርጋቸው እንደሁላችን ሰው ነውና በፈሪዎች በትር የሚደርስበት አካላዊ ስቃይ ግን ለህዝባችን የገባነውን ቃል ውሳኒያችንን እና አቋማችንን እንደብረት ያጠነክረዋል እንጂ አያላላውም።ይልቁንም በአንዳርጋቸው መታፈን ምክንያት ከመላ ሀገራችን በአለም ዙሪያ ከተበተነው ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የነሰታነት ሃይሎች የምንሰማውና እየሰማን ያለነው የሚያስገመግም ህብረ ድምጽ ከብረት የሚያጠነክር ሃይል ሆኖኗል።
አንዳርጋቸው የዘራው የነጻነት የአርበኝነት ዘር ከመብቀል አልፎ እየጎመራ በመሄድ ላይ ነው። አንዳርጋቸው ሺ አንዳርጋቸውን ተክቷል። ወያኔ አንዳርጋቸውን በማፈንና በእጁ አስገብቶ በራሱ መስኮት ቲቪ ስቃዩን እንግልቱን በማሳየት ሊያላምጠው የማይችል የብረት እንክብል ነው የነከሰው። ይህንንም ሳይውል ሳያድር ያየዋል፡፡
መላው ህዝባችን በእልህና በቁጭት ላይ ያለህ ወገናችን ና የሀገራችን የነሰታነትና የዴሞክራሲ ሃይሎች በሙሉ፡- በአንዳርጋቸው ላይ ወያኔ የፈጸመው የአሸባሪዎች ውንብድና በየአንዳንዳችን ላይ የተፈጸመ በደል ግፍ ነው።
ይህንን የሽብርና የውንብድና ስርአት ለማስወገድ አብረን ከመነሳት ውጪ አማራጪ የለንም። የልዩነታችንን አጥር አፍርሰን የወየኔን እድሜ እንድናሳጥር ግንቦት 7 ለሁላችንም ጥሪውን ያቀርባል።
አንድ ሆነን የአንዳርጋቸውን ስምና ምግባር እንሁን!
አንዳርጋቸው የዘራው እና እየጎመራ ያለው የአርበኝነት ንቅናቄ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ወያኔ አንዳርጋቸውን ያፈነበት ቀን የሚረግምበት ጊዜ ከዚህ በኋላ ሩቅ አይሆንም፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

ከግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ

                                             

ከግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ
ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን!!!

ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም
በየጊዜው እየከረረና እየገረረ የመጣው ትግላችን “ሁላችን አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ወደ ተባለ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ይህ ጽሁፍ የዚህን የትግል ምዕራፍ ምንነትና ይዘት በአጭሩ ያብራራል። በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈሩት ዓረፍተ ነገሮች ተነበው የሚታለፉ ሳይሆን በተግባር የሚተረጎሙ ሥራዎች ናቸው።
አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ምን ማለት ነው? አንዳርጋቸው ጽጌ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት በጀግንነት የቆመ፤ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ሲከፍል የነበረና አሁንም እየከፈለ ያለ መሪያችን ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ልክ እንደሱ ትሁት ሆኖም ግን ቆራጥ፤ ሆደ ሰፊ በዚያው ልክ ደግሞ መራር፤ አስተዋይና ብልህ ሆኖም ተግባር ተኮር መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ወያኔን ለማስወገድ መደረግ የሚገባውን እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀ ሰው መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ለአገርና ለትውልድ ቤዛ መሆን ማለት ነው።
ወያኔ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ካተኮረባቸው ምክንያቶች አንዱ የወያኔን የዘር ፓለቲካና ፕሮፖጋንዳ በሚያመክን መልኩ በተግባር ትግል ውስጥ ካሉ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ እና ሌሎች ዘውግ ተኮር ድርጅቶች ጋር ንቅናቄዓችን ተግባራዊ ትብብር ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ድረስ ማቀራረብ የቻለ መሪ መሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ለወያኔ የጉሮሮ ቁስል የሆነበት ደግሞ ከትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጋር ግንቦት 7 የፈጠረው ጠንካራ ትብብር ነው። በትህዴን ጋር በመሆን አቶ አንዳርጋቸው ወያኔ በትግራይ ሕዝብ ጀርባ መንጠልጠል እንዳይችል አድርጎታል። እናም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ከዘረኝነት ፀድቶ መገኘት ማለትም ጭምር ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት በኢትዮጵያዊያን እኩልነት እና እኩል ባለመብትነት ከልብ ማመን እና ለእኩልነት በጽናት መታገል ማለት ነው።
አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን የግድ የግንቦት 7 አባል መሆንን አይጠየቅም። አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን ለመልካም ዓላማዎች መሳካት ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀትን እንጂ የግድ ከአንድ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር መወገንን አያሻም። ያም ሆኖ ግን አንዳርጋቸው ጽጌን የሆነ ሰው በጠንካራ ድርጅት የታገዘ ትግል አስፈላጊነት ይረዳል።
በመጨረሻም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ኦኪሎ ኦኴኝ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና እዚህ ዘርዝረን ልንጨርሳቸው የማንችላቸው ጀግኖቻችንን ሁሉ መሆን ማለት ነው።
“የሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ዘመቻ ትኩረቶችን በየጊዜው የምንገልጽ ሲሆን ከነገ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋል ያለበት የዓለም ዓቀፍ ዘመቻው የመጀመሪያ እርከን ትኩረቶች በዚህ በታች ቀርበዋል
የዘመቻው የመጀመሪያው እርከን ትኩረቶች
ይህ የመጀመሪያ እርከን ሶስት ቦታዎች ላይ ያተኩራል፡- የመን፣ ብርታኒያ እና ወያኔ
የመንን በተመለከተ
የየመን መንግሥት የዓለም ዓቀፍ ህግም ሆነ የየመን የራሷን ህግ በመተላለፍ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ለየመን መንግሥት የተደረገው ተማጽኖ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። እስካሁንም ድረስ የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውን ማሠሩና ለወያኔ አሳልፎ መስጠቱ በይፋ አላመነም። እኛ ባለን መረጃ መሠረት በአይሮፕላን ማረፊያው ከማገት ጀምሮ በልዩ በረራ ወደ ኢትዮጵያ እስከ መላክ ድረስ ያለውን የውንብድና ሥራ በየመን በኩል ሆኖ የሠራው ቀጥታ ተጠሪነቱ ለየመን ፕሬዚዳንት የሆነው የስለላ ድርጅት ነው። በዚህም ሳቢያ የየመን መንግሥት ሊቀለበስ የማይችል እና በቀላሉ የማይፋቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የየመን መንግሥትና ሕዝብ ይህን እንዲያውቁት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የተግባር እንቅስቃሴ አካል ነው።
የመንን በተመለከተ የሚቀጥለው ሳምንት ዘመቻችን ግብ ቁጣችንን የየመን ፕሬዚዳንት እና የየመን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የየመን ሕዝብም እንዲያውቅ ማድረግ ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ያህል ተጠቅሰዋል።
  1. ለየመን ፕሬዚዳንት አዲስ መረር ያለ ደብዳቤ ተጽፎ በፋክስና በኢሜል በየመን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች አድራሻዎች መላክ። በመልዕክት መጨናነቅ ከሚገባቸው የየመን ተቋማት አንዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የየመን ኤምባሲ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆናችሁ በዘመቻው የምትሳተፉ ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ እናሳስባለን፤ የኢንተርኔትና የፋክስ መልክቶችን ስትልኩ ራስን ለጉዳት በማያጋልጥ መንገድ መደረግ ይኖርበታል።
  2. የየመን ኤምባሲዎችን ሥራ ማወክ በሚችሉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ማጨናነቅ። የፕሬዚዳንቱን ፎቶና የአገሪቱን ባንዲራ ማቃጠል። ይህ በውጭ አገራት ብቻ መደረግ ያለበት ነው።
  3. በውጭ አገራት በየከተሞች ለሚገኙ የየመን ኮሚኒቲዎች ደብዳቤ መፃፍና መንግሥታቸውን እንዲቃወሙ መገፋፋት፤ ይህንን ካላደረጉ ግን ከመንግሥታቸው ጎን ተሰልፈው በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዳወጁ የምንቆጥረው መሆኑን በማያሻማ መንገድ መንገር፤
  4. በየመን አየር መንገድና በማናቸው የየመን የንግድ ድርጅቶችና ቢዝነሶች ላይ እቀባ ማድረግ፤ በቢዝነሶቻቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማድረግ። ይህ ተግባር በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያ ውጭም በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መተግበር የሚኖርበት አቢይ ተግባር ነው።
  5. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የየመን ቢዝነሶችን መርጦ ምርቶቻቸው እና አገልግሎቶቻቸው እንዲጠሉ ማድረግ። ከእንግዲህ በየመን ገንዘብ የተሠራ ወይም ከየመን የመጣ ብስኩትም ይሁን ሲጃራ የወገናች ደም የነካው እቃ ነው።
 ብርታኒያን በተመለከተ
የእንግሊዝ መንግሥት ማድረግ የነበረበትን እና ማድረግ ይችል የነበረውን ሁሉ አድርጓል ብለን አናምንም። እርምጃው ፈጣን አልነበረም፤ አሁንም አይደለም።
ስለሆነም እንግሊዝን በተመለከተ የዘመቻችን ግብ የእንግሊዝ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈጉ መክሰስ እና ከአሁን በኋላም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለውና መሪያችን እንዲያስፈታ መወትወት ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ተዘርዝረዋል።
  1.  የእንግሊዝ መንግሥትን በህግ መክሰስ (ይህ በንቅናቄው ጽ/ቤት የሚሠራ ሲሆን ዝርዝሩ ወደፊት ይገለፃል)፤
  2. ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ደብዳቤ ጽፎ በፋክስና በኢሜል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ለኤምባሲዎች በብዛት መላክ። አንዱ ትኩረት የሚደረግበት ኤምባሲ አዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዘመቻው የሚሳተፉ ወገኖች አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
  3. በለንደን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደጃፍ፤ በሌሎች አገሮች ደግሞ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች ቁጣ የተቀላቀለበት የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄድ።
 ወያኔን በተመለከተ
ወያኔን በተመለከተ የሚደረጉ ትግሎች በሙሉ ወያኔን ከስልጣን ማስወገድን ያነጣጠሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ወያኔም ለመጣል ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ፡ ከቁም ውርደትና ባርነት ለነጻነትና ለፍትህ ከወያኔ ጋር ጉረሮ ለጉረሮ እየተናነቁ እየጣሉ ለመውደቅ ፤ መስዋእት ለመሆን በወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንና የህዝብ ሃይሎች የሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቅሴ ነው ፤ እንቀላቀላቸው።
በተለያዩ ምክንያቶች ወሳኙን ትግል መቀላቀል የማይችሉ ወገኖቻችን በያሉበት ሆነው ከወያኔ የስለላ መረብ ተጠነቅቀው ራሳቸውን በቡድን ያደራጁ፤ ይህንኑ የሚያግዙ ተግባራት ለመፈጸም ራሳቸውን ያዘጋጁ። እነዚህ ተግባራት ወያኔን በገቡበት እየገቡ በማሳፈር ፤እረፍት በመንሳት፤ የፈፀሟቸውን ወንጀሎች በአደባባይ በመናገር እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤ ማንነታቸው ለሸሪኮቻቸው ወይም ለሥራ ባልደረቦቻቸው በመንገር ወዳጅ በማሳጣት፣ ንግዶቻቸውን ኩባንያዎቻቸው እንዲከስሩ በማድረግ የፋናንስ አቅማቸው በማዳከም ረገድ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ከዚህ አኳያ ሊደረጉ ከሚገቡ ተግባራት የሚከተሉት በምሳሌነት ተዘርዝረዋል።
  1. በምዕራቡ ዓለም በተለያዩ ሽፋኖች ተሰግስገው ያሉት እና የሚመላለሱ ወንጀለኞች የወያኔ ሹማምንትና ደጋፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ መደራጀትና እንደየሀገሩ ሁኔታ አግባብ ያላቸውን የህግ መሳሪያዎች መጠቀም፤
  2. በመላው ዓለም የወያኔ ኤምባሲዎችና የኮንሱላር ጽ/ቤቶች ሥራ መሥራት የማይችሉበት ሁኔታ መፍጠር፤
  3. በመላው ዓለም የወያኔ አባላትና ደጋፊዎችን ከያሉበት (ከሰፈር፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በንግድ የተሰማሩ ..) በማደን ማስነወር፣ ማግለል፣ ማዋረድ፤ ከእነሱ ጋር አንዳችም የንግድም ፡ የሥራ ፤ የማኅበራዊ ትብብርና ግንኙነት አለማድረግ፤ ፊት መንሳት ፤ በሥራዎቻቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳዎችን ማካሄድ። የወያኔ አባላትንና ደጋፊዎችን በሁሉም ዓይነት ግንኙት ማግለል፡ አለመተባበር በኢትዮጵያም ውስጥ በስፋት በሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል።
  4. በማናቸውም የዓለም ክፍል ለሥራ ወይም ለሽርሽር የሚዘዋወሩ ከፍተኛ የወያኔ ሲቪል፣ የወታደራዊና የደህነት ባለሥልጣኖችና የጦር መኮንኖችን እየተከታተሉ ማሸማቀቅ፣ ማስነወር፣ መውጫ መግቢያ ማሳጣት፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይነት እንደሌላቸው በሕዝብ ላይ ለፈጸሙት ወንጀሎች ሁሉ የሕዝብ ቁጣ ዒላማ እንዲሆኑ እንደልባቸው መፏላል እንዳይችሉ ማድረግ። በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ ራሱ በቡድን አደራጅቶ ለወያኔ ታጣቂዎች ጥቃት ሳያጋልጡ አድብቶና አስልቶ ተመሳሳይ ድርጊቶች መፈፀም
  5. የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በወያኔ አገዛዝ የሚመሩ እንዲሁም በወያኔ ኤፈርት ስር ያሉ ኩባንያዎች፤ቢዝነሶች ላይ እቅባ ማድረግ፤ የሸቀጥና የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ አለመሆን፤ በእነሱ ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማድረግ፤ በልዩ ልዩ መንገዶች ሥራቸውን ማጨናገፍ ማደናቀፍ፤ አሻጥሮችን በተደራጀ መልክ፣ በጥናትና በብልሃት ተግባራዊ ማድረግ። ይህ በኢትዮጵያም በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተግባሪዊ መደረግ ይኖርበታል።
  6. በዌስተር ዩኒየን፣ በመኒ ግራም እንዲሁም በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ በወያኔ ደጋፊዎች በመሠርቱዋቸው ልዩ ልዩ የገንዘብ ላኪ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ አለመላክ፤ በየአካባቢው አማራጭ የገንዘብ መላኪያ መንገዶችን መፈለግ፤ እነዚህ በሌሉባቸው አካባቢዎች የፈጠራ ችሎታን በመጠቀም ገንዘብ ለዘመድ አዝማድ በወያኔ በኩል ሳይላክ የሚደርስበትን ሁኔታ መፍጠር፤ የወያኔን የፋሽታዊ አገዛዝ አንዱና ዋነኛ ምሰሶ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ የማድረቂያ ዘዴዎችን ሁሉ በመፈለግ ተግባሪዊ በማድርግ የወያኔን በዘረኝነትና በዘረፋ የተገነባ የገንዘብና የኢኮኖሚ አቅም ማዳከም፤ መቦርቦር፤ መናድ።
  7. ከወያኔ ጋር የሚሠሩ የውጭ አገር ድርጅቶች ከወያኔ ጋር ያ ያላቸውን ሽርክና እንዲያቋርጡ መወትወት፤ አልሰማ ካሉ በቢዝነሳቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማካሄድ። (የእነዚህን ዝርዝሮች በተከታታይ ይገልጻሉ)
  8. የምዕራብ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግኑኝነት እንዲመረምሩ ማሳሰብ። በተለይ ደግሞ ሳያስተምሩ ለወያኔ ሹማምንቶች ዲግሪ የሚያድሉ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችን ማስጠንቀቅ፤ ተግባሮቻቸውን ለተማሪዎቻቸው ጭምር መንገር (ለምሳሌ University of Greenwich ከ International Leadership Institute ጋር ያለውን ግኑኝነት እንዲሰርዝ፣ እስከዛሬ የሰጣቸውንም የማስትሬት ዲግሪዎች እንዲመረመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፎ በብዛት በፋክስ መላክ፤ ተመሳሳይ ደብዳቤ Open University እና ከወያኔ ጋር ተሻርከው ለሚሠሩ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች መላክ)
  9. ይህ ዘመቻ ለጊዜው በወያኔ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም፣ የሕዝቡን የነፃነትና የፍትህ ጥረት የሚያደናቅፉ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች በሆኑ ቱጆሮችና ከወያኔ ጋር የተያያዙ የንግድ ቤቶችና ኩባንያዎች የዘመቻው ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዝርዝራቸውን በተከታታይ እናወጣለን)
በመጨረሻም የወጣቱ የማያልቅ የፈጠራ ችሎታ ከላይ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ ሆኖም ግን ውጤታማ የሆኑ የተቃውሞ መግለጫ ዘዴዎች ያፈልቃል ብለን እናምናለን። ስለሆነም ዘመቻውን በየአካባቢው በሚገኝ ሀሳብና ፈጠራ ማዳበር ይቻላል። ይህ ዘመቻ ወያኔ ከስልጣን እስኪባረር ድረስ በየጊዜ እየከረረ መሄድ እንዳለበት ታሳቢ አድርጎ መነሳት ይኖርበታል። ስለሆነም በየጊዜው አዳዲስ ነጥቦችን ተግባሪዊ የትግል ስልቶችን እንጨምራለን።
ለመላው የአትዮጵያ ሕዝብ፣ በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሁሉ በኅብረት በጋራ ሆነን፤ ትከሻ ገጥመን ለተግባሪዊ ትግል በቁርጠኝነት እንድንነሳ ጥሪያችንን እናቀርባለን ።
ይህ ዘመቻ ወያኔን ከስልጣን ለማባረር ምድር ላይ ከምናደርገው የመረረ ትግል ጋር ሲቀናጅ የሚፈለገውን ውጤት ስለሚያስገኝ ለነፃነቱ ግድ ያለው ዜጋ ሁሉ በሙሉ ኃይሉና አቅሙ ተሳትፎ እንዲያደርግ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራዊ ጥሪ ያቀርባል።
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!


እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ!

አንድን ሰዉ ጀግና የሚያሰኙ ብዙ መለኪያዎች አሉ፤ የእነዚህ መመዘኛዎች ስፋትና ጥልቀት ደግሞ እንደያገሩ ባህልና ወግ ይለያያል። የጀግንነት ትልቁ መለኪያ ጦር ሜዳ ዘምቶ ጠላትን ቁጭ ብድግ እያሰኙ መቅጣት ነዉ ብለዉ በሚያምኑ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገሮች ዉስጥ “ ጀግንነት” የሚለዉን ጽንሰ ሀሳብ ጽንሰ ሀሳቡ በሚነካካዉ ሁሉም መልኩ መግለጽ አስቸጋሪ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ ግን በዬትኛዉም አገርና ባህል አንድን ሰዉ ጀግና ሊያሰኙ የሚችሉ መስፈርቶችን በሙሉ ከወጣትነት ዘመኑ ጀምሮ ያሟላ ሙሉ ህይወቱን ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ አሳልፎ የሰጠ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነዉ። አገርህን አድን እያልንም ሆነ ወይም በርዕዮተአለም እየቀሰቀስን እልፍ አዕላፋትን ወደ ጦር ሜዳ ማዝመት ተችሏል፤ ለወደፊትም ይቻላል። ግን ይህ ስራ በራሱ ብዙም ጀግንነት የሚጠይቅ ስራ አይደለም። ለጦርነት ከቀሰቀስናችዉ ሰዎች ጎን ተሰልፈን ጦር ሜዳ ድረስ መዝመት ግን እሱ አሱ ወደር የለሽ ጀግንነት ነዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ የነጻነትና የፍትህ አርበኞችን ያፈራ ብቻ ሳይሆን እሱ እራሱ አንደ አንድ አርበኛ ዉግያዉ ወረዳ ድረስ ሄዶ አብሯቸዉ ሊዋደቅ የተዘጋጀ ቆራጥ ሰዉ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ፍትህ በሌለባቸዉ ቦታዎች መኖርን የሚጸየፍ ፍትህን የቀመሙትን ሰዎች ወይም ተቋሞች ደግሞ ባሉበት ቦታ ሁሉ በጽናት የሚታገል አሁንም የፍትህና የነጻነት ጠላቶች በመታገል ላይ እንዳለ በየመን ከሀዲዎች አዉሮፕላን ጣቢያ ዉስጥ ታግቶ ለወያኔ ዘረኞች ተላልፎ የተሰጠ ዘመን ስራዉን የማያደበዝዘዉ ጀግናና የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ጽጌ ዕድሜዉ ከሃያ አመት በታች ከነበረበት ግዜ አንስቶ የፊዉዳሉን ስርዐት፤ የደርግን ስርዐት ዛሬ ደግሞ የዘረኞችን ስርዐት የተቃወመ ብቻ ሳይሆን የተፋለመ እዉነተኛ ጀግና ነዉ። አብረዉት ትግል የጀመሩ ግለሰቦች የራሳቸዉ ህይወት ከህዝብ አደራ በልጦባቸዉ ከትግል አለም ሲለዩ፤ አንዳንዶች በቃን ደከመን ብለዉ ወኔ ሲከዳቸዉ ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለስልጣንና ግዜያዊ ጥቅም ሚኒልክ ቤ/መንግስትን ከተቆጣጠረ ሁሉ ጋር ቤተኛ ሲሆኑ አንዳርጋቸዉ ግን በአካሉም በመንፈሱም ያልተሸነፈ፤ ለገንዘብም ለስልጣንም ሲል ህሊናዉን ያልሸጠ ህዝብና አገር የሰጡትን የፍትህና የነጻነት አደራ እንደተሸከመ ከአርባ አመታት በላይ ጸንቶ የቆመ እዉነተኛ የነጻነት አርበኛ ነዉ። እንዳርጋቸዉ ጀግና ብቻ ሳይሆን በዘመናት ዉስጥ አንዴ ብቅ ብለዉ ሰማይን በብርሃን አድምቀዉ አንደሚሰወሩ ሰማያዊ አካላት ወይም ከዋክብት ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያዉያን በድፍረት የነጻነት ችቦ የለኮሰ የህዝብ ባለአደራ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የሆኑት የወያኔ ዘረኞችም ይህንን የህዝብ ልጅ አፍሪካ አዉሮፓና መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥ በየሄደበት የተከታተሉትና በመጨረሻም እነሱን በመሳሰሉ ከሀዲ መንግስታት አማካይነት እንዲያዝ ያደረጉት አንዳርጋቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የለኮሰዉ የፍትህና የነጻነት ችቦ እንደሚያጋልጣቸዉ ብቻ ሳይሆን ጠራርጎ እንደሚያጠፋቸዉም ስለሚያዉቁ ነዉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ “እባብን መመታት ጭንቅላቱን ነዉ” የሚባል የቆየ አባባል አለ። በእርግጥም እባብን ለመግደል ከጭንቅላቱ የበለጠ ጉዳት የሚያደርስበት ሌላ ቦታ የለም። ሆኖም እዚህ ላይ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ፤ እሱም እባብን ጭንቅላቱን መትተን ስንገድለዉ የሚሞተዉ አንድ እባብ ብቻ ነዉ፤ ብዙ እባቦች በህይወት ይኖራሉ፤ አዳደሶች ደግሞ ይወለዳሉ። ጅሎቹ የወያኔ ዘረኞች “እባብን መምታት” በሚለዉ ተረት ተሞኝተዉ አንዳርጋቸዉን ይዘዉ በማሰቃየት ወይም በመግደል ህዝባዊ ትግሉን አኮላሽተነዋል ብለዉ አስበዉ ከሆነ እጅግ በጣም ተሳስተዋል። የወያኔ ዘረኞች አንዳርጋቸዉን አሰሩ አላሰሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱን መታገሉን የሚያቆመዉ መብቱን፤ ነጻነቱንና የአገሩን አንድነት ለሱ ለራሱ ዉሳኔ ሲተዉለት ብቻ ነዉ። የሰዉ ልጅ እባብን መቀጥቀጡን የሚያቆመዉ እባብ መናደፉን ሲያቆም ብቻ ነዉ፤ የወያኔም ነገር እንደዚሁ ነዉ፤ ዘረኝነቱን፤ መብት ረጋጭነቱንና የአገር ድንበር መሸርሸሩን እስካላቆመ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ይታገለዋል ፤ መታገል ብቻ ሳይሆን የሚገባዉን ቅጣት ይሰጠዋል።
የወያኔ ዘረኞች እነሱ በእራሳቸዉ ሞክረዉ ሞክረዉ ያቃታቸዉን ነገር በዉንብድናና በክህደት እነሱን ከሚመስል የሌላ አገር መንግስት ጋር በመተባበር አንዳርጋቸዉ በህገወጥ መንገድ ታግቶ በህገወጥ መንገድ እጃቸዉ ዉስጥ እንዲገባ በማድረግ ለግዜዉም ቢሆን አንዳርጋቸዉን ከትግሉ ሜዳና ከትግል ጓደኞቹ ነጥለዉት ይሆናል፤ ሆኖም ግን የአንዳርጋቸዉ መታሰር በተሰማበት በአጭር ግዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ ዉስጥና ከኢትዮጵያ ዉጭ እልፍ አዕላፋት ጀግኖች በቅጽበት ተፈጥረዉ አንዳርጋቸዉ ያበራዉን ችቦ አንግበዉ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያሉ ትግሉን ተቀላቅለዋል።
ወያኔና የመን በመመሳጠር በጋራ አስረዉ የሚያሰቃዩት አንዳርጋቸዉ ጽጌ ሰነዓ ላይ ሲታሰርና ለወያኔ ተላልፎ ሲሰጥ አንድ ብቻዉን ነበር። ዛሬ ግን በየመኖች መታገቱና ለወያኔ ተላልፎ መሰጠቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ በገባ ሳምንት በማይሞላዉ ግዜ አንድ ብቻዉን የታሰረዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ብለዉ እስከ መጨረሻዉ ወያንን ለመፋለም የቆረጡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቆራጥ ኢትዮጵያዉያንን ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል። ዛሬ ከዉጭዉ አለም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባዉና ከኢትዮጵያ ወደ ዉጪዉ አለም የሚወጣዉ ድምጽ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” የሚል የትግል ጥሪ ድምጽ ነዉ።
አንዳርጋቸዉን በህገወጥ መንገድ አግተዉ ለወያኔ ያሰረከቡት የመኖችም ሆኑ ዘረኞቹ የወያኔ ባለስልጣኖች አንዳርጋቸዉ ዬት አንዳለ አናዉቅም ብለዉ አይክዱ ክህደት ክደዉ ነበር፤ ሆኖም አዉነትን ደብቀዉ ማቆየት እንደማይችሉ ስለተረዱ አንዳርጋቸዉን ለሁለት ሳምንታት ያክል ሲቀጠቅጡ ከቆዩ በኋላ ባለፈዉ ማክሰኞ አንዳርጋቸዉ እጃቸዉ ላይ እንደሚገኝ አምነዋል። በጥላቻ ተወልደዉ በጥላቻ ያደጉት የወያኔ መሪዎች አንዳርጋቸዉ ጽጌን የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል ስለሆነ ብቻ አይደለም እንደዚህ አክርረዉ የሚጠሉት። አንዳርጋቸዉ ለነጻነቱና ለእናት አገሩ ደር ድንበር መከበር አጥብቆ የሚሞግትና ሌሎችም እንደሱ ለነጻነታቸዉና ለአገራቸዉ አንድነት እንዲሟገቱ የሚገፋፋ የመብት፤ የነጻነትና የአገር አንድነት ጠበቃ ነዉ። ለዚህ ነዉ ይህንን የአገር አለኝታ የሆነ ሰዉ እስክ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ድረስ የሚሆን ገንዘብ ለየመኖች ሰጥተዉ ታግቶ እንዲሰጣቸዉ ያደረጉት።
የወያኔ ዘረኞች ይህንን አገርና የወገን አለኝታ የሆነ ሰዉ አስረዉ የሰዉ ልጅ አይቶትም ሰምቶትም የማያዉቀዉን ሰቆቃ ሁሉ እንደሚያወርዱበት ጥርጥር የለንም።አንዳርጋቸዉ ጽጌ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብት፤ ነጻነትና የግዛት አንድነት መከበር ህይወቴ ታልፋለች ብሎ በአንድ ህይወቱ የተወራረደ ሰዉ ነዉ፡ እንደተናገረዉም ቃሉንም ያከበረ ሰዉ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ይህንን ጀግና ሰዉ ባሰቃዩና የስቃይ ድራማቸዉን በዚያ እንደ ቤት ዉስጥ ዕቃችዉ በሚቆጣጠሩት ቴሌቪዥን ላይ ባሳዩን ቁጥር ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር በቁጣና በእልህ ተነሳስተን “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያልን ትግሉን መቀላቀል ነዉ እንጂ አንገታችንን ደፍተን እነዚህ ዘረኞች እንድንሆንላቸዉ የሚፈልጉትን መሆን የለብንም።ህዝባዊ ትግሉ አምርሯል፤ ትንቅንቁ ተጀምሯል። ጎንበስ ቀና እያለ እንደ ህፃን ልጅ በእንብርክኩ ይጓዝ የነበረዉ የቱኒዝያ አብዮት በሁለት እግሩ ቆሞ እንዲሄድ መሐመድ ቦአዚዝ እራሱን መስዋዕት አድርጎ ማቅርብ ነበረበት። አይነካም አይሞከርም ሲባል የነበረዉን ሞባረክን በ15 ቀናት ከስልጣን አባርሮ ለፍርድ ያቀረበዉ የግብጹ አብዮት ከዳር ዳር እንዲቀጣጠል የሃያ ስምንት አመቱ ወጣት ከሊል መሐመድ ሰይድ መሞት ብቻ ሳይሆን አንደ ክትፎ መከታተፍ ነበረበት።
ኢትዮጵያን የሚጠብቅ አይተኛምና ለእኛም እንደ ሙሴ መርቶ ወደ ተስፋዉ አገር እንዲያደርሰን አንዳርጋቸዉ ጽጌን አድሎናል። አንዳርጋቸዉ ልክ እንደ ሙሴ የታገለለትን ማየት አይችል ይሆናል- እሱ የታገለለት አላማ ግን ምንም ጥርጥር የለንም ግቡን ይመታል። አንዳርጋቸዉ ከአርባ አመታት በላይ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለእኩልነት የታገለዉ አልበቃ ብሎት እራሱን መስዋዕት አድርጎ አቅርቦልናል፤ በዚህ ጀግና ሰዉ መስዋዕትነት የማይቀሰቀስና ትግሉን በቀጥታ የማይቀላቀል ኢትዮጵያዊ ካለ እሱ ከክብር ዉርደትን፤ ከነጻነት ዉርደትን የሚወድ ደሙ ከደማችን ያልተቀላቀለ ሰዉ መሆን አለበት። እኔ አንዳርጋቸዉ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ፤ አገሩን ኢትዮጵያን የሚወድ ኢትዮጵያዊ፤ ጉልበትና አቅም ያለዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህንን አንዳርጋቸዉ የጀመረዉን ትገል ነገ ሳይሆን ዛሬዉኑ መቀላቀል አገራዊ ግዴታዉ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ ጽጌ ወያኔን መቃወም ብቻ ሳይሆን ከመቃወም አልፎ የወያኔን ሰርዐት ለማሰወገድ ዱርቤቴ ብሎ በአይን የሚታይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረና የጀመረዉን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ወያኔን ፊት ለፊት ተፋልሞ ማስወገድ በሚችልበት አስተማማኝ ቦታ ላይ ያደረሰ ቆራጥና ደከመኝን የማያዉቅ ጀግና ነዉ።ለዚህ ነዉ የአንዳርጋቸዉ እንቅስቃሴ እንቅልፍ የነሳዉ ወያኔ በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመንግስታት ደረጃ ተመሳጥሮ ይህንን ጀግና ሰዉ በህገ ወጥ መንገድ በዉንብድና የያዘዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ ደብዝዞ የነበረዉን ህዝባዊ ትግል ህይወት የዘራበት እሱ አራሱ ግን አንደ ሻማ የቀለጠ እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደ ቱኒዝያዉ ቦዚኦዚዝና እንደ ግብጹ ከሊድ ልንመለከተዉ የሚገባን የትግላችን አቀጣጣይ ችቦ የሆነ ሰዉ ነዉ። ዛሬ አንዳርጋቸዉ የሚፈልገዉና የሚመኘዉ በመታሰሩ ከንፈራችንን እየመጠጥን እንድንዘናጋና ሀሞታችን እንዲፈስ አይደለም። ይልቁንም የሱ ምኞትና ፍላጎት በሱ መታሰርና ስቃይ የእኛ ክንድ እንዲበረታና ሞራላችን እናሸንፋለን በሚል ጥርጥር የለሌለዉ ጽኑ ፍላጎት እንዲገነባ ነዉ።የአንዳርጋቸዉ ፍላጎት ቀፎዉ አንደተነካበት ንብ ‘ሆ’ ብለን ተነስተን እሱንና ሌሎች ተቆጥረዉ የማያልቁ ዜጎቻችንን የሚገድሉትንና እያሰሩ የሚያሰቃዩትን የወያኔ ዘረኞች ከአገራችን ምድር ጠራርገን እንድናጠፋ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ እንደ ብዙዎቻችን አባት አለዉ፤ እናት አለዉ፤ ባለትዳርና የልጆች አባት ነዉ፤ ወንድም፤ እህትና ጓደኞችም አሉት። እሱ ግን ከእናቱ፤ ከአባቱ፤ ከልጆቹና ከትዳሩ አገሬ ኢትዮጵያ ትበልጥብኛለች ብሎ የአዉሮፓን ትኩስ ምግብና የተሞናሞነ ህይወት ምን ሊሆነኝ ብሎ ምግብና ዉሃ ብርቅ ወደ ሆነበት በረሃ ሄዶ ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ ጠንካራ መሠረት ያኖረ ሰዉ ነዉ። አንዳርጋቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀግና ያለህ ብሎ ለግማሽ ምዕተ አመት አርግዞ በጣር የወለደዉ የቁርጥ ቀን ልጁ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ወያኔ ሃያ ሶስት አመት ሙሉ በዘር፤ በቋንቋ፤ በከልልና በሃይማኖት ሲከፋፍል የከረመዉን ህዝብ ካልሰበሰብኩ እንዳለ እንደ ወጣ የቀረ ጀግናችን ነዉ፡፡ አዎ አንዳርጋቸዉ እንደ ስሙ አንድ ሊያደርገን ጎንበስ ቀና ሲል የለየላቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች እጅ ወድቋል። አንዳርጋቸዉን የምንወድና የአንዳርጋቸዉ በድንገት ከትግል ሜዳ መለየት ያንገበገብን በብዙ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ኢትዮጵያዉያን ወደድንም ጠላን ዛሬ ያለን ምርጫ ከወያኔ ጋር ተናንቀን እኛንም አገራችንንም ነጻ ማዉጣት ወይም በወያኔ እየተረገጥን ልጆቻችንን፤ ጓደኞቻችንንና ወዳጅ ዘመዶቻችንን ተራ በተራ እየገበርን መኖር ብቻ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ዛሬ እጁ በዘረኞች ተይዞ የሚሰቃየዉ ከባርነት ነጻነት፤ በግሉ ከሚያገኘዉ ህብትና ብልጽግና የአገሩ ህልዉና በልጦበት ነዉ። አንዳርጋቸዉንና አገሬን የምንል ኢትዮጵያዉያን ከዛሬ በኋላ ይህ አንዳርጋቸዉ ያቀጣጠለዉ ህዝባዊ ትግል ወያኔንና ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት እስካልደመሰስ ድረስ ለአንድም ቀን ቢሆን እንቅልፍ ሊወስደን አይገባም። አንዳርጋቸዉ የሂሊናም ሆነ የአካል እረፍት አግኝቶ እፎይ የሚለዉ እሱ ከወያኔ ቁጥጥር ስር ነጻ ሲወጣ አይደለም። አንዳርጋቸዉ እፎይ ብሎ የሰላም እንቅልፍ የሚተኛዉ እሱ የጀመረዉን የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጉዞ እኛ ስንጨርስለት ብቻ ነዉ። ስለዚህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፤ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፤ እዉቀት ያለህ ደግሞ በእዉቀትህ ነገ ዛሬ ሳትል ይህንን ትግል ተቀላቀል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!