Monday, 22 September 2014

የተመድ ኤክስፐርቶች ኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ትጠቀማለች ሲሉ ከሰሱ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ሁሉን አቀፍ የአቻ ለአቻ ግምገማ የውሳኔ ሐሳቦችን ለመገምገም የተሰበሰበው የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ቡድን መስከረም 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በጀኔቭ ስዊዘርላንድ ባደረገው ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብረተኝነት አዋጁን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብትን ለመጣስ መጠቀሙን እንዲያቆም አሳሰበ፡፡ 
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ሪፖርትና የሰብዓዊ መብት ይዞታን በአገሪቱ ለማሻሻል የተወሰዱትን ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ተከትሎ፣ አባል አገሮች የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ያደጉ አገሮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲሻሻል ወይም እንዲሰረዝ የጠየቁት ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ነው፡፡ 
የፀረ ሽብርተኝነት ሕግና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የመደራጀትና የሰላማዊ ስብሰባ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የዳኞችና የጠበቆች ነፃነትና የኢሰብዓዊ አያያዝና ክብርን የሚያዋርድ ቅጣት መብቶች ልዩ ራፖርተሮች የሆኑት ቤን ኤመርሰን፣ ማይና ካያ፣ ዴቪድ ካዬ፣ ሚቸል ፎርስት፣ ጋብሪኤላ ክናውልና ጁአን ሜንዴዝ በጋራ ያወጡት ሪፖርት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያ የወጡ ሪፖርቶች ማመላከታቸውን ይገልጻል፡፡ ‹‹ግርፋትና ኢሰብዓዊ አያያዝ በኢትዮጵያ ማቆያዎች ውስጥ መስተዋሉ ከፍተኛ የመሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤›› ሲልም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
የኤክስፐርቶች ቡድኑ ሽብርተኝነትን መዋጋት አስፈላጊ ድርጊት ቢሆንም፣ ትግሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መሥፈርቶችን ሳይጣረስ መከናወን እንዳለበት ግን አስምሮበታል፡፡ ‹‹ፀረ ሽብርተኝነትን የሚደነግጉ አንቀጾች በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግጋት ውስጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መተርጎም አለባቸው፡፡ ሕጎቹም ላልተገባ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውሉ አይገባም፤›› ሲልም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
ሪፖርቱ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የተከሰሱ ግለሰቦች ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሒደት እያገኙ እንዳልሆነም ይወቅሳል፡፡ በተለይም ከሕግ አማካሪዎችና ከጠበቆች ጋር የመገናኘት መብት እንደማይተገበርም ያስረዳል፡፡ ‹‹ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሒደት የማግኘት መብት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የመደራጀት መብት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አፈጻጸም መጣሳቸው ቀጥሏል፤›› ሲሉም ኤክስፐርቶቹ ያሳስባሉ፡፡ 
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም በዘፈቀደ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ሁሉንም ሰዎች እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት መሪዎች መደበኛና ሕጋዊ ሥራቸውን ያለ ዛቻና እስር ሳይፈሩ እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል፤›› ሲሉም የተመድ ኤክስፐርቶች ጠይቀዋል፡፡ ኤክስፐርቶቹ ኢትዮጵያ የአዋጁን አፈጻጸም ከገባቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ጋር እያገናዘበች እንድታስኬድም ጥሪ አድርገዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመቃወም የሕዝብ ፊርማ እስከማሰባሰብ የደረሰው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር) ሪፖርቱን አስመልከቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ፓርቲያችን አንድነት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የሕግ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድ ነው ያለው ከየትኛውም ፓርቲ ቀድሞ ነው፡፡ አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ከኢሕአዴግ የተለየ አቋም የሚያንፀባርቁ ግለሰቦችና ጋዜጠኞችን ለማፈን ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ግዛቸው የሕጉን ተፅዕኖ በማየት ፓርቲያቸው በ2005 እና በ2006 ዓ.ም. ሕጉን ለማሰረዝ ፊርማ የማሰባሰብ ሥራ መሥራቱንም አስታውሰዋል፡፡
የተመድ ኤክስፐርቶች ሪፖርት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ምን ያህል ጠቃሚ ነው በሚል የተጠየቁት አቶ ግዛቸው፣ ተመድ ሕጉ ጉድለት አለበት ስላለ ሳይሆን አዋጁ ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ፓርቲያቸው ተቃውሞውን እንደጀመረ ገልጸዋል፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብታቸው በሕገ መንግሥቱ ቢከበርም እነዚህን መብቶች በመጣስ በሕጉ አማካይነት በርካታ የህሊና እስረኞችን ኢትዮጵያ እንዳፈራችም አመልክተዋል፡፡ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል የሚሉ ከሆነ ለምን ጥያቄአቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ለሕገ መንግሥታዊ አጣሪ ጉባዔ እንዳላቀረቡ የተጠየቁት አቶ ግዛቸው፣ ከሕግ ክፍላቸው ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነና በቅርቡ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አንድነት ፓርቲ ሁሉ በአዋጁ ላይ የሰላ ተቃውሞ በማቅረብ የሚታወቀው የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የኤክስፐርቶቹ ሪፖርት የፓርቲያቸውን አቋም እንደሚያንፀባርቅ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም በሪፖርቱ በጣም ደስተኛ ነን፡፡ ኤክስፐርቶቹ ገለልተኛና በጉዳዮቹ ላይ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ ተዓማኒነት ያለው ሪፖርትም በማውጣት ይታወቃሉ፡፡ ይኼ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ከመፍጠር አልፎ ተግባራዊ ዕርምጃ ለመውሰድም የሚያስችል ተፅዕኖ ይፈጥራል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከነሐሴ 22 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ተጠቅሶ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተከሰው ፍርድ ያገኙ ሲሆን፣ በቅርቡም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በዚሁ አዋጅ ተከሰው ጉዳያቸው በመታየት ላይ ነው፡፡ መንግሥት ግን ይሠሩት ከነበረው ሙያዊ እንቅስቃሴ ባሻገር በሽብር ተግባር ሲሳተፉ እንደያዛቸው በመግለጽ ራሱን ይከላከላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የህሊና እስረኛ እንደሌለ መግለጻቸውን ባለፈው ረቡዕ ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡   
 

Thursday, 4 September 2014

ወጣቱን ለማደንቆር ያለመው ስልጠና ህወሓትን ለመቅበሪያነት ይዋል!

                                     
የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በየቦታው ሰብስቦ እያሰለጠነ ነው። ይህ ሲያልቅ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስልጠና ይቀጥላል ተብሏል። በድምሩ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣት አንድ አይነት ሰነድ አንብቦ ለ2007 ትምህርት ይዘጋጃል ማለት ነው። ስልጠናው ወደ መንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ይስፋፋል ተብሎ ይገመታል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በዚህ ሥልጠና ላይ ያለውን እይታ በነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓም ቁጥር 328 ርዕሰ አንቀጹ መግለጹ ይታወሳል። ግንቦት 7 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት መድፈራቸው ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ተገንዝቦ ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት እንዲታገዝ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ መክሯል። ሆኖም ግን ህወሓት ለስልጠናው የሰጠው ትኩረት ቀድሞ ከታሰበው በላይ በመሆኑ ንቅናቄዓችን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደገና ሊመለስበት ወስኗል።
ህወሓት፣ ይህንን ያህል መጠነ ሰፊ ስልጠና ማድረግ ለምን አስፈለገው? የዲሞክራሲ ኃይሎችስ ይህንን ስልጠና እንዴት ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ?
ህወሓት ይህንን ትርጉም የለሽ ስልጠና በአሁኑ ሰዓት ለመስጠት የፈለገበትን በርካታ ምክንያቶች ማቅረብ ቢቻልም የሚከተሉት ሁለቱ ግን ዋነኛዎቹ ናቸው ብለን እናምናለን።
አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ህወሓት የተከታዮች ድርቅ የደረሰበት መሆኑ አድርባይ መሪዎቹን ማሳሰቡ ነው። በሚሊዮን ይቆጠራሉ የሚባሉት የኢህአዴግ አባላት ልባቸው ከህወሓት ጋር አለመሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ደግሞ በተላላኪዎቹ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደህዴግ የተሰባሰቡ አባላት በግልጽ ህወሓትን መቃወም እየጀመሩ ነው። ህወሓት የራሱን መጥፊያ እያደራጀ መሆኑ የተሰማው በመሆኑ አዳዲስ “ምዕመናንን” ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ መመልመል ይፈልጋል። የመንግሥት ንብረትና መዋቅር ለፓርቲ ስልጠና የሚጠቀም በመሆኑ ከብዛት የሚገኝ ትንሽም ቢሆን ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ የወጭው ጉዳይ ህወሓትን አያሳስበውም። ስለሆነም ይህ ስልጠና በተቻለ መጠን ብዛት ያላቸዉን የተማተሩ ወጣቶች በአድርባይነት ለህወሓት ማሰለፍን አላማዉ አድርጎ የተነሳ ስልጠና ነዉ።
ሁለተኛው አቢይ ምክንያት ደግሞ ህወሓት ለኢትዮጵያ ወጣት ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ወደ እያንዳንዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ጆሮ መድረሱን ማረጋገጥ መፈለጉ ነው። መልዕክቱም “ሜዳ ውስጥ ያለሁት ተጫዋች እኔ ብቻ ነኝ። ለሚቀጥሉት አርባና አምሳ ዓመታትም እኔን የሚገዳደረኝ አይኖርም፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ ለለውጥ ያለህ ተስፋ ከንቱ ነው። አርፈህ ቁጭ ብለህ ተገዛ” የሚል መልክት ነው።
ስልጠናዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ዓላማዎችን በሚገባ ማስፈፀም ይችላሉ ብሎ መገመት ከባድ ነው። የስልጠናው ይዘት እጅግ የወረደ እና የሰልጣኞቹን ብስለት ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ መሆኑ ስልጠናውን ምፀት የበዛበት አድርጎታል፤ አሰልጣኞቹንም ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል። የስልጠናዎቹ ጽሁፎች (ማንዋሎች) ይዘት ደግሞ የአዘጋጆቹ የእውቀት ማነስ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑ ለተማሪዎቹ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሆነውላቸዋል። በአጠቃላይ ስልጠናው ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ያልተዘጋጁበት ፈተና ደቅኖባቸዋል። የኢትዮጵያ ወጣት ሲሞሉት የሚሞላ ባዶ ጋን አለመሆኑን እያዩት ነው። ወጣቶች ጠጣር ጥያቄዎችን ያነሱባቸዋል፤ አሰልጣኖች እነዚህ ጥያቄዎች እንዴት መመለስ እንዳለባቸው ስለማያውቁ ይደናበራሉ። መልስ ሲጠፋ ቁጣ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ይከተላል።
ይህም ሆኖ እነዚህ ስልጠናዎች ለህወሓት ምንም ውጤት አያስገኙም ብሎ ማለፍ አይቻልም። የስልጠናዎቹ ውጤት የሚወሰነው ግን የኢትዮጵያ ወጣት ከህወሓት ውጭ ለሚመጣ መረጃ ባለው ቅርበት መጠን ነው። ሁሉም የመረጃ ምንጮች ተዘግተውበት የህወሓትን የእድገትና የሰላም መዝሙር ሲሰማ ለኖረ ሰው በስልጠናው የሚሰጡ ባዶ ፕሮፖጋንዳዎችን የመቃወሚያ ምክንያት አይኖረውም። ለተለያዩ የመረጃ ምንጮች ቅርበት ያለው ወጣት ግን የህወሓት መዝሙር ከግራዚያኒ የእድገትና የሰላም መዝሙር የተለየ አለመሆኑን ይረዳል። በፋሺስት ወረራ ወቅት ግራዚያኒም ኢትዮጵያን በመንገድና በህንፃ እየገነባሁ ነው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አውሮፓ የደረሰችበት ደረጃ ላይ አደርሳታለሁ ይል እንደነበር ይታወሳል።
የህወሓትን ኢትዮጵያን ለአርባና አምሳ ዓመታት የመግዛት እቅድን ወጣቱ ምክንያታዊ ነው ብሎ ይቀበላል? የራሱን አፋኝ ህጎች አክብረው እየተፍጨረጨሩ ያሉ ተቀናቃኖቹን እንኳን በእንጭጩ እየደፈጠጠ ያለ ሥርዓት “ኃላፊነት የሚሸከም አጣሁ” የሚለው ሰበቡ በወጣቱ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል? በግንቦት 7 እምነት ይኸኛው የስልጠና ዓላማ ሊሳካ የሚችለው በዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ድክመት ብቻ ነው። ዘረኛውንና ዘራፊውን ወያኔ መጣል ብቻ ሳይሆን ከወያኔ በኋላ ፍትህ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሚሰፍኑበትን ስትራቴጄ ያዘጋጀና ለስትራቴጂዉ ክንዉንራሱን ያዘጋጀ ድርጅት መኖሩን የኢትዮጵያ ወጣት ማወቅ ይኖርበታል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሌሎች ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ወደ ነፃነት፣ እኩልነትና ብልጽግና ጎዳና ለማስገባት እየታገለ መሆኑን ሁሉም ወጣት ሊገነዘብ ይገባል። ይህ ግንዛቤ ካለ የኢትዮጵያ ወጣት ለእብርተኛው፣ ዘረኛው፣ ሙሰኛውና ከፋፋዩ ህወሓት ተገዢ አይሆንም።
በስልት ከተጠቀምንበት ህወሓት ብዙ ሚሊዮኖች የሕዝብ ገንዘብ አውጥቶበት ያዘጋጀው ስልጠና ለራሱ ከሚሰጠው ጥቅም በላይ ለዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ይበልጣል። ለምሳሌ፣ ግንቦት 7 እነዚህን ስልጠናዎች የኢትዮጵያን ወጣት ለትግል ያላቸውን ዝግጁነት ለመገምገም ተጠቅሞበታል። “የኢትዮጵያ ወጣት ለትግል ዝግጁ ነው – የቀረው ድርጅት ነው” ሲል የግምገማውን ውጤት አሳውቋል። በዚህም ርዕሰ አንቀጽ ይህንኑ መልዕክት ማስረጽ ይፈልጋል።
በአምባገነን ሥርዓቶች ውስጥ የሚኖሩ ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች ከተለመዱ አደረጃጀቾች መለየት አለባቸው። መደበኛ (Formal) አደረጃጀቶች አባላትን ለአደጋ ያጋልጣሉ። በዚህም ምክንያት ነው ግንቦት 7፣ ኢ-መደበኛ (Non Formal) አደረጃጀቶች የሚመርጠው። በእኛ ሁኔታ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” ስንል አራት ይሁን አምስት የሚተማመኑ ወጣቶች የሚፈጥሩት የግንቦት 7 ሴል ነው። ይህንን ሴል የፈለጉትን ስም ሊሰጡት ይችላሉ – እድር፣ ክበብ፣ የሆነ ስፓርት ቡድን ደጋፊ የተመቻቸውን ስያሜ ይስጡት። የተቋቋመበት ዓላማ ግን ግልጽ ነው – ለፍትህና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ማገዝ ነው። ይህ ኢ-መደበኛ ስብስብ ራሱን የግንቦት 7 አካል አድርጎ ይቁጠር። የግንቦት 7 ፕሮግራሞችንና ጽሁፎችን ያንብብ። ስብስቡ ለመረጃዎች ራሱን ቅርብ ያድርግ። መረጃዎችን ይለዋወጥ። በሂደት ቀጣዩ መንገድ ግልጽ እየሆነለት ይመጣል።
እየተካሄደ ያለው የህወሓት የጅምላ ስልጠና ለኢ-መደበኛ ድርጅቶች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች እነዚህን ስልጠናዎች የግንቦት 7 ሴሎችን ለማደራጀት እንዲጠቀሙበት እንመክራለን። ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ወጣት የፈጠራ ችሎታ ላይ እምነት አለው። የኢትዮጵያ ወጣት አደንቁሮ ሊቀብረው የመጣውን ስልጠና ህወሓትን ለመቅበሪያነት እንደሚጠቀምበት የግንቦት 7 እምነት ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

በተማሪዎች ላይ የኃይል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተገለጸ

በትምህርት በኢህአዴግ ጽ/ቤትና በትምህርት ሚኒስትር ትብብር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚሰጠው ስልጠና በተማሪዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተገልጾአል፡፡ በስልጠናው ሰነድ ላይም ተካትቷል፡፡ ‹‹የትምህርት ተቋማትን ወደ ትክክለኛው የትግል ስልት የመመለስ አስፈላነት›› በሚል አብይ ጉዳይ ላይ በተሳሳተ ስልት ይንቀሳቀሱ እንደነበር በመጥቀስ ‹‹ተማሪው ጥያቄውን የሚያቀርበው ትምህርቱን እየተማረ፣ የትምህርት ቤቱን ህግና ደንቦች እያከበረ ሊሆን ይገባል፡፡…..ህገ ወጥ ሆኖ ህጋዊ ምላሽ ማግኘት አይቻልም፡፡›› በሚል ‹‹ህገ ወጥ ከሆኑ›› ህገ ወጥ ምልሽ እንደሚጠብቃቸው ያስጠነቅቃል፡፡
UNiversity students
ሰንዱ አክሎም ‹‹በተማሪው ማህበረሰብ ውስጥ አፍራሽ አዝማሚያ ያላቸው ተማሪዎች ነውጥን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በጥብቅ በመታልና የንብረት ውድመት እንዳይደርስ በጥብቅ መታል ይገባል፡፡ በቅድሚያ ራስን መነጠል እና ቀጥሎም የነውጥ ኃይል አራማጅና ደጋፊ የሆኑትን ማጋለጥና ትግል ማድረግ ይገባል›› በሚል በተማሪዎቹ ላይ ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ ይዘረዝራል፡፡
ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ